ጤና ይስጥልን ተወዳጆች!
በአለፈው ሳምንት ነቅዐ-ሕይወት አብነት ትምህርት ቤትን ለመጎብኘት እድሉ ገጥሞን ነበር።በእዚህም ቆይታችን የሚከተሉትን መልካም ተስፋዎችን አይተን ተመልሰናል።
1.  ጉባኤ ቤቱ ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ በመጻሕፍት ትርጓሜ ሲያስተምራቸው የነበሩትን ሃያ ስምንት ደቀመዛሙርት እግዚአብሔር ቢፈቅድ የካቲት አስር ለማስመረቅ ቀን ተቆርጧል። 


2.  ተመራቂ ተማሪዎች ጋር በአደረግነው ውይይት ነገ ለቤተክርስቲያን በምን መልክ ማገልገል እንደአሰቡ አብራርተውልን ነበር። ከእዚህም የተረዳንው የአስተማረቻቸውን ቅድስት ቤተክርስቲያን ሁሉም በተለያየ ስልት ለማገልገል በእዚያ ደረጃ ማቀዳቸው የተሰጣቸው ትምህርት የመጻሕፍት ትርጓሜ ብቻ ሳይሆን ሕይወትን ለእግዚአብሔር አሳልፎ መስጠትን መሆኑን ለመረዳት ችለናል።ይኽም ብዙዎቻችን ስንመኘው የነበረ የእውነተኛ አገልጋዮች ርእይ ነው።

3.  አሁን የምንአየውን የቤተክርስቲያን ችግር ለመፍታት ሌላው መንገድ ህጻናትን ከልጅነታቸው ጀምሮ በቃለ እግዚአብሔር ኮትኩቶ ማሳደግ ነው።ይኽንንም እውን ለማድረግ አንድ መነኩሴ አባት የአካባቢውን ህጻናት በማሰባሰብ ንባብ፣ ግብረ-ዲቁና እና የስነምግባር ትምህርት እየአስተማሩ ይገኛሉ። ይኽ ትምህርት ከተጀመረ ከዓመት በላይ ሲሆን አእምሮአቸው እግዚአብሔርን በመፍራት የተሳለ እና ለመቀደስ የደረሱ ታዳጊዎችን ማፍራት ተችሏል።
4.  ደቀመዛሙርቱ በእለተ-ሰንበታት በየገጠር አቢያተ ክርስቲያናት ለስብከተ ወንጌል በመፋጠን ብዙ ነፍሳትን ወደ እግዚአብሔር መንገድ በመመለስ ላይ ይገኛሉ።
5.  ጉባኤ ቤቱ በስነምግባር ጉድለት ሕይወታቸው ከእግዚአብሔር መንገድ የተለዩትን የማኅበረሰብ ክፍሎችን ለመመለስ “ዕቅበተ-አዕምሮ” የሚባል ወርኃዊ ጉባኤ ወለህ እና ሰቆጣ ከተማ ላይ በማዘጋጀት የምእመናንን ሕይወት እየታደገ ይገኛል።
6.  ሰንበት ትምህርት ቤቶችን በማቅረብ በህብረት ቤተክርስቲያንን እንዲያገለግሉ ለማስቻል በጉባኤ ቤቱ ስብከተ-ወንጌል እያከናወነ ይገኛል።
ከእዚህም አልፎ ሰንበት ትምህርት ቤት በአልተቋቋመባቸው አድባራት እንዲቋቋም እየተደረገ ነው።

7.  በሰቆጣ ከተማ የመማሪያ ክፍሎችን በመከራየት ከ6-13 እድሜ የአላቸውን ታዳጊዎች የቀለም ትምህርት ማጠናከሪያ(ሒሳብ እና አማርኛ) እየሰጠ ይገኛል። ከእዚህም በተጨማሪ ስነ ምግባር እና መዝሙር የሚማሩ ሲሆን ትምህርቱም የሚሰጠው ረቡዕ ዐርብ ቅዳሜ እና እሁድ ነው። ተማሪዎቹ በጎበኘናቸው ወቅት የተማሩትን የአካፈሉን ሲሆን ሙሉ የተቀረጸውን ቪዲዮ ለታዳጊዎች ብታሳዩአቸው ይጠቀማሉ። ከአስተማሩን ትምህርት የሚከተለውን በጽሑፍ ለማቅረብ ወደድን።

ኦርቶዶክሳዊ መልካም እሴቶች የሚባሉት፡-
1.  አለባበስ
2.  አመጋገብ
3.  አነጋገር
4.  አረማመድ
5.  ፍቅረ እግዚአብሔር
6.  ፍቅረ ሰብእ
7.  የመንፈስ ፍሬዎች
8.  ኦሮቶዶክሳዊ ግዴታዎች
ኦርቶዶክሳዊ ግዴታዎች የሚባሉት፡-
1.  ጾም
2.  ጸሎት
3.  ስግደት
4.  በዓላት
5.  ምግባር
6.  አስራት
8.  በእለተ-ሰንበት በወህኒ ቤት የሚገኙትን ወገኖች በመጎብኘት ቃለ-እግዚአብሔር እንዲማሩ እየተደረገ ነው።
9.  በሱስ የተጠቁትን በቃለ-እግዚአብሔር ለማከም ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
10.  ከተለያዩ የዞኑ ወረዳዎች የሚመጡ በሥራ ላይ የአሉ ክርስቲያኖችን በክረምት ወቅት ለአንድ ወር ተከታታይ ትምህርት ይሰጣል።
11.  መሬት በመከራየት ጉባኤ ቤቱ ሽንብራ እና ሽንኩርት በመስኖ እያመረተ ይገኛል።

ጉባኤ ቤቱ የአሉበት ችግሮች፡-
1.  ጉባኤ ቤቱ የተከፈተው 2011ዓ.ም. ነው። በእዚያን ወቅት ጠቅላይ ቤተ-ክህነት ለ10 ተማሪዎች፤ ለእያንዳዳቸው የቀለብ 400 ብር መድቦ እስከአሁን እየረዳ ይገኛል። አሁን 40 ተማሪዎች የሚገኙ ሲሆን ማኅበረ-ቅዱሳን ደግሞ ለ10 ተማሪዎች 600 ብር እየደጎመ ይገኛል። የተቀሩት ተማሪዎች በጉባኤ ቤቱ ተጠሪ እና መምህር በሆኑት አባት ጥረት ከምእመናን በሚገኝ ድጋፍ በቂ የማይባል ደረጃ ምግብ እየቀረበላቸው ይገኛል። ከ2014 ዓም የታየው የኑሮ ውድነት ቤተክርስቲያንን ለመዋጀት እየደከመ የሚገኘውን ጉባኤ ቤት ከፍተኛ ችግር ላይ ስለጣለው የተማሪ ቀለብ በነፍስ ወከፍ በመቻል እንድንደግፈው ጥሪ እናስተላልፋለን። 
2.  የጉባኤ ቤቱን የአስገነባው ኅዋስ(ኮሚቴ) ለለተማሪዎቹ ጥቃቅን ወጪዎች(ሳሙና፣የጽሕፈት መሣሪያ መግዣ፣ ወዘተ) መሸፈኛ በጎ አድራጊዎችን በማስተባበር ለመምህራን 300 ብር እንዲሁም ለተማሪዎች 150 ብር እየደጎመ ይገኛል። ይኽም ከአለው የኑሮ ውድነት የተነሳ በቂ ስለአልሆነ ክፍያን መጨመር ይፈልጋል።
3.  ጉባኤ ቤቱ የሚያገኘው የመብራት ኃይል አነስተኛ በመሆኑ ምግብ የሚዘጋጀው በእንጨት ስለሆነ ለማገዶ መግዣ በዓመት ከ200000 ብር የአላነሰ ወጪ እያወጣ ይገኛል። ይኽንን ወጪ ለማስቀረት ትራንስፎመር መግባት የአለበት ሲሆን ይኽንንም ለማድረግ 850000 ብር የአስፈልጋል።
4.  ሐዋሪያዊ አገልግሎቱ ከመስፋቱ የተነሳ ጉባኤ ቤቱ አሽከርካሪ የሚፈልግበት ደረጃ ላይ ደርሷል።እንዲሁም በጣም ገጠራማ ቦታዎች ላይ የሚያገለግል ቻርጅ የሚደረግ የድምጽ ማጉያም እንደሚያስፈልገው ተረድተናል።
5.  የጉባኤ ቤቱ መረቃ በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት እስከአሁን አልተደረገም። ይኽንንም ከተማሪዎች ምረቃ ጋር ለማድረግ ታስቧል። በጦርነቱ ወቅት ህንጻው ጉዳት ደርሶበት ነበር። እንዲሁም የአልተጠናቀቁ ስራዎችን ጨርሶ የእናንተ የጉባኤ ቤቱ ቤተሰቦች ድጋፍ የአስፈለጋል። የወጪው ዝርዝር እንደሚከተለው ቀርቧል።

6.  ለተማሪዎች መገልገያ የሚሆኑ ሰባት ቁምሳጥኖች እና 14 የጠረጴዛዎች ማሟላት ይገባል።

ማጠቃለያ
ጉባኤ ቤትን መደገፍ ራስን መደገፍ ነው። ጉባኤ ቤት መደገፍ ሃይማኖታችንን ለመጪው ትውልድ  በቀደመ ክብሯ ማስተላለፍ ነው። ስለእዚህ በምንችለው ሁሉ ድጋፋችን እንዳይለይ አደራ እንላለን።

ድጋፍ የምታደርጉ የሚከተለውን አድራሻ መጠቀም ትችላላችሁ
0935 363693 / 0911 460813 
ወለህ ደብረገነት ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ልማት ኮሚቴ
የሂሳብ ቁጥር  1000085335751(ንግድ ባንክ)

Comments powered by CComment