የመስቀል ክብር
የኦርቶዶክስና የፕሮቴስታንት የልዩነት ነጥብ የኦርቶዶክስ ኃይማኖት ለመስቀል የምትሰጠው ክብር ነው፡፡ፕሮቴስታንቶች ከጸሎት በፊት ወይንም በኋላ በስም አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ በማለት በመስቀል አምሳያ (በትእምርተ መስቀል )አያማትቡም ሰዎችን ወይም አልባሳትን ለመባረክ መስቀልን አይጠቀሙም፡፡ ፕሮቴስታንቶች መስቀልን በልባችን አናመልካለን ይላሉ ፡፡እሰከ ቅርብ ጊዜም ድረስ በቤተ ክርስቲያናቸው ላይ መስቀል አያደርጉም ነበር፤ብዙዎቹ ማተብ አያስሩም ፤አንዳቸውም በእጃቸው መስቀል አይዙም፡፡ የመስቀልን በዓል አያከብሩም በተጨማሪም እየዘመሩና እያመሰገኑ መስቀል ይዘው አይሰለፉም መስቀል አይሳለሙም በመስቀልም ቡራኬ አይቀበሉም ፡፡ ኦርቶዶክስ ለምን ይህን ሁሉ ክብር ለመስቀል እንደሰጠች ለመግለጽ እንሞክራለን ፤በተጨማሪም ማማተብ ጠቃሚ አስፈላጊና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምሕርት መሆኑን እናያለን፡፡

 
፩ኛ.የጌታችን ትኩረት በመስቀል ላይ
ጌታችን በአገልግሎቱ ወቅት (ከመሰቀሉ በፊት) ለመስቀል ታላቅ ትኩረት ሰጥቷል ፡፡ይህንንም ሲገልጽ "መስቀሉን የማይዝ በኋላዬም የማይከተለኝ የእኔ ሊሆን አይገባውም፡፡"ማቴ 10፡38 እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ"ማር 8፡34አለ፡፡ ከወጣቱ ሀብታም ጋር ባደረገው ንግግርም "መስቀሉንም ተሸክመህ ና ተከተለኝ ማር “10፡21በማለት የመስቀሉን ታላቅነት አስረዳ ፡፡በተጨማሪም "ማንም መሰቀሉን ተሸክሞ በኋላዬ የማይመጣ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም፡፡"ሉቃ 14፡27 አለ፡፡ ስለዚህ በመስቀል አምሳያ ባማተብን ጊዜ ጌታችን ያስተማረንን ትምህትና ያዘዘንን ትዕዛዝ እናስታውስበታለንና እናማትባለን፡፡
፪ኛ.መስቀል የመላዕክትና የሐዋርያት የአገልግሎታቸው መሰረት ነው፡፡
የጌታችንን መነሳት ለሴቶቹ ያበሰረው መልአክ "እናንተስ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁና ማቴ 28፤5-6 አለ፡፡ጌታችን የተነሳ ቢሆንም መልአኩ ጌታችንን የተሰቀለው ብሎእንደ ጠራው ልብ እንበል፡፡ታዲያ የተሰቀለው የሚለውን ስም ጌታችን ከተነሣ በኋላ እንኳ ተጠርቶበታል፡፡ከመላዕክቱም በተጨማሪ አባቶቻችን በስብከቶቻቸው ለጌታችን መስቀል ትኩረት ሰጥተዋል፡፡ይኸውም ቅዱስ ጴጥሮስ አይሁድን ሲሰብክ እንዲህ ብሏል "እንግዲህ እናንተ የሰቀላችሁት ኢየሱስን፡ እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ "ሐዋ 2፡36 አለ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም "የጌታ መስቀል እንደማሰናከያና እንደሞኝነት ቢቆጠርም እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስ እንሰብካለን" 1ቆሮ 2፤23 አለ፡፡ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ መልቀልን የክርስትና መሰረት አድርጎ ይቆጥረዋል፡፤ይህንንም "ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር እርሱም እንደ ተሰቀለ እንጂ ሌላ ነገር እንዳላውቅ ቆርጬ ነበረና "1ቆሮ 2፡2 በማለት አስረዳ፡፡ ስለዚህ እኛም በማተብን ጊዜ የመላዕክቱና የሐዋርያቱ መሠረት የሆነውን የመስቀልን ነገር እያስታወስን፣ለሰውም እንዲያውቅ እያደረግን ነውና እናማትባለን፡፡
፫መስቀል የሐዋርያት ክብራቸው ነበር፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ "ከጌታችን ከኢየሱስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ" ገላ 6፤14 አለ፡፡ ከነዚህ ቃላት ጀርባ ያለው ምስጢር ምን እንደሆነ ብንጠይቀው ደግሞ እንዲህ ይለናል፦ "ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልኩበት" ገላ 6፤14 በማለት ይመልስልናል፡፡ስለዚህ እኛም ስናማትብ መስቀል የሐዋርያቱ ክብራቸው እንደነበረ እያሰብን የኛም ክብራችን ሞገሳችን እንዲሆን እራሳችንን እያለማመድን መሆናችን ይሰማናልና እናማትባለን፡፡
፬.ስናማትብ የመስቀልን ሰማያዊና መለኮታዊ ትርጉሞች እናስታውሳለን፡፡
ስናማትብ ጌታችን ለኛ ያለውን ፍቅር ስለኛ መዳን የተቀበለውን ሞት እናስታውሳለን ኢሳይያስም ስለዚህ ሲያብራራ "እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በርሱ ላይ አኖረ፡፡"ኢሳ 53፡6 አለ ፡፡ ዮሐንስም እንዲሁ "እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ "ዮሐ 1፤29አለ፡፡በሌላም ቦታ"እርሱም የኃጢአታችን ማስተስርያ ነው፡፡"1ዮሐ 2፤2 አለ፡፡ሰለዚህ ስናማትብ የመስቀልን ሰማያዊነት ማለትም በመስቀል የተደረገልንን የኃጢአት ስርየት እናስታውስበታለንና እናማትባለን፡፡
፭.በመስቀል አምሳያ ስናማትብ በመስቀል ላይ የተሰቀለው ገንዘቦች መሆናችንን እንገልጻልን፡፡
በማማተብ፣ መስቀልን አንገት ላይ በማሰር፣ በጌጣጌጦቻችን በመቅረጽ፣ በእምነት ቦታዎቻችን ላይ ከፍ አድርገን በመስቀል፣ ለእኛ የተሰቀለው የኢየሱስ ክርስቶስ ወገን መሆናችንን በግልጽ እናውጃለን፡፡ ስለ ክርስቶስ መስቀል በሰዎች ፊት አናፍርም ፡፡ነገር ግን በእርሱ እንከብራለን እርሱን የሙጥኝ እንላለን፡፡ ስለዚህ እኛ በቃላችን ሳንናገር ሰዎች እኛን በማየታቸው ብቻ ስለ እምነታችን የተሰበኩ ይሆናሉና በመስቀል አምሳያ እናማትባለን፡፡
፮ኛ.ሰው መንፈስና አእምሮ ብቻ አይደለም ነገር ግን አካለዊ ስሜት ያለውም ጭምር እንጂ ስለዚህም መስቀልን ከላይ በገለጥናቸው ሁኔታዎች በስሜቱ ሊረዳ ይገባል፡፡ አእምሮ እራሱ መስቀልን ሊያውቅና ሊያስታውስ አይችልም ፡፡ነገር ግን በስሜቱ ሲያየውና ሲዳስሰው መስቀልንና በመስቀል ላይ የተፈጸመውን የተሰቀለውን ያስታውሳል፡፡ስለዚህም በመንፈስ በአእምሮና በአካል እግዚአብሔርን እናመልካለን ፡፡አካላዊ ስሜቶችም መንፈሳችንና አእምሮአችን እንዲያመልክ ያግዙታል፡፡ስናማትብ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ እንላለን እንጂ ዝም ብለን አናማትብም ስለዚህ ባማተብን ቁጥር እስከ ዘለዓለም አንድ አምላክ በሆነ በቅድስት ሥላሴ ማመናችንን እንገለጻለን ፡፡ይህም ያለማቋረጥ ቅድስት ሥላሴን እንድናስብ እድል ይሰጠናል በመስቀል አምሳያ እናማትባለን፡፡
፯.ስናማትብ በሥጋዌና በተደረገልን ካሣ ማመናችንን እንመሰክራለን፡፡
ስናማትብ እጃችንን ከላይ ወደታች ከግራ ወደ ቀኝ በመውሰድ እናማትባለን በዚህም እጃችንን ከግንባራችን ወደ ደረታችን ስናወርድ እግዚአብሔር ከሰማያት መውረዱን እናስባለን፡፡እጃችንን ከግራ ትከሻችን ወደ ቀኝ ትከሻችን ስንወስድ ደግሞ ሰዎችን ከግራ ወደ ቀኝ ከጨለማ ወደ ብርሃን ማሻገሩን እናስታውሳለን፡፡ታዲያ ስናማትብ ለልባችን የሚሰሙት መንፈሳዊ ስሜቶች እጅግ ብዙ ናቸው በጌታችን በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ ወደምድር መውረድ (በልዕልና ከሚኖርበት አምላካዊ አኗኗር ሰውን ለማዳን ሲል ትሁት ሰብእናን ፊል 2፥1-9)፡፡ገንዘብ በማድረጉ እርሱ ተዋርዶ እኛን ማክበሩን እርሱ ምድራዊ አካልን ተዋህዶ እኛ ከሱ የተነሳ ሰማያውያን እንዳደረገን፡፡ከሲኦል ወደ ገነት ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሀን ያሸጋገረን መሆኑን ያስታውሰናልና በመስቀል አምሳያ እናማትባለን፡፡
፷.በትእምርተ መስቀል አምሳያ ማማተብ ለህፃናቶቻችን እንዲሁም ለሌሎች ሰዎች የኃይማኖት ትምህርት ነው፡፡ሲጸልይ ወደ ቤተክርስቲያን ሲገባ ሲተኛና በሁሉም ጊዜ የሚያማትብ ሰው ሁል ጊዜ መስቀልን የሚያስታውስ ነው፡፡ ይህም ትውስታ ጠቃሚ መንፈሳዊና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ነው፡፡ እርሱም ሰዎችን ያስተምራል ፡፡በተለይ ህፃናትን ስለ ክርስቶስ መስቀል እንዲያውቁ ያደርጋቸዋልና በተእምርተ መስቀል አምሳያ እናማትባለን፡፡
፱.ስናማትብ ክርስቶስ ስለኛ መሞቱን እንገልጻለን፡፡ጌታ ደግሞ እስከሚመጣ ድረስ ስለኛ የተደረገውን ሞቱን መመስከር የጌታ ትዕዛዝ ነው ፡፡1ቆሮ 11፤26 ስለዚህ ባማተብን ቁጥር ሞቱን እናስታውሳለን ፡፤የጌታን መሞት በቅዱስ ቁርባንም ጭምር እናስታውሳለን፡፤ ሆኖም ቅዱስ ቁርባንበሁሉም ቦታና ጊዜ አይደረግም ፡፡ማማተብ ግን በሁሉም ቦታና ጊዜ ሊደረግ ስለሚችል የጌታን ሞት በሁሉም ቦታ እና ጊዜ በማማተብ ልናስታውስ እንችላለን የጌታችንን ሞት ለማስታወስ እናማትባለን፡፡
፲.ስናማትብ የኃጢአት ደመወዝ ሞት እንደሆነ እናስታውሳለን፡፡ስለኛ በደል ጌታችን በመስቀል ተሰቅሎ ሞቶ ሕይወትን ሰጠን፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ "ከወደደን ከፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳን በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወትን ሰጠን" ኤፌ 2፤5አለ ጌታችን በመስቀል ዋጋውን ከፈለና አባቱን አባት ሆይ ይቅር በላቸው አለ፡፡ ስለዚህ ስናማትብ አዳም እጸበለስን እንዳትበላ ተብሎ ታዞ ሳለ የአምላኩን ቃል አቃሎ ና ተደፋፍሮ እጸበለስን በመብላት ኃጢአትን ቢሰራ ለኃጢአቱ ደመወዝ(የልፋትህ ውጤት) ይሁንህ ተብሎ የተሰጠው ሞት ነውና ያንን ሞት ለማጥፋት ያለ በደሉ የተሰቀለውን የጌታችንን መስቀል እያሰብን በትእምረተ መስቀል ባማተብን ጊዜ ሁሉ ኃጢአትን ብንሰራና በኃጢአታችን ብንጸና እድል ፈንታችን ጽዋ ተርታችን የኃጢአታችን ደመ ወዝ የሞት ሞት መሆኑን አውቀን ኃጢአትን ከሐስራት እንቆጠብበታለንና በትእምርተ መስቀል አምሳያእናማትባለን፡፡
፲፩ኛ.በመስቀል ስናማትብ እግዚአብሔር ለኛ ያለውን ፍቅር እናስታውሳለን፡፡
መስቀል የፍቅር መስዋዕት እንደሆነ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል "በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና ፡፡"ዮሐ 3፤16 ፡፡ቅዱስ ጳውሎስም "ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለኛ ሞቷልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር የራሱን ፍቅር አስረዳን፡፡ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቀን ይልቁንም ከታረቀን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን፡፡"ሮሜ 5፤8 በማለት ነገረን፡፡ በመስቀል እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅሩን እናስታውሳለን፡፡ምክንያቱም "ነፍሱን ስለወዳጆቹ ከማኖር ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅርለማንም የለውም፡፡"ዮሐ 15፤13 ስለዚህ ስናማትብ እግዚአብሔር እኛን የወደደበት የፍቅር መጠን በመስቀል ተሰቅሎ እስከመሞት ያደረሰው መሆኑን ያስታውሰናልና በትእምርተ መስቀል አምሳያ እናማትባለን፡፡
፲፪.ኃይልን ስለምናገኝ በመስቀል አምሳያ እናማትባለን፡፡ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ "የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነው ፡፡ "1ቆሮ 1፡18 አለ፡፡ እዚህ ላይ መስቀል የእግዚአብሔር ኃይል ነው አለ እንጂ ፣ የእግዚአብሔር ኃይል መስቀል ነው አላላም፡፡እኛም ስናማትብ በኃይል እንሞላለን ፡፡ጌታችን በመስቀል ሞትንና ሰይጣንን ድል አድርጎ ሕይወትን ለሰዎች ሁሉ ሰጥቶአልና፡፡መንፈሳዊ ኃይል ገንዘብ እናደርግ ዘንድ በትእምርተ መስቀል አምሳያ እናማትባለን፡፡
፲፫.ሰይጣን ስለሚፈራው እናማትባለን፡፡
ከአዳም ጀምሮ የተደረገው የሰይጣን ትግል በመስቀል ከንቱ ሆነ፡፡እግዚአብሔር በደሙ ዋጋውን ከፍሎ የሰዎችን ኃጢአት አስተሰረየ ፡፡ለሚያምኑትና ለሚታዘዙት ሁሉ ሕይወትን ሰጣቸው ፡፡ስለዚህም ሰይጣን መስቀል ባየ ቁጥር በመስቀል ኃይል የተደረገውን ታላቁን መዋረዱን መሸነፉንና ያጣውን ምርኮ በማስታወስ ይሸሻል ፡፡ስለዚህ የእግዚአብሔር ልጆች በትእምርተ መስቀል ያማትባሉ፡፡ ምክንያቱም መስቀል የድል ምልክት ነውና ባማተቡ ጊዜ የእግዚአብሔር ኃይል በውስጣቸው ይሞላል ፡፡ጠላትም ከውስጣቸው ይሸሻል ፡፡በሙሴ ዘመን ለሰዎች ከበሽታና ከሞት መዳን ምክንያት የሆነው የእባብ መስቀል የክብር ባለቤት የሆነውን የክርስቶስን መስቀል ይመስላል ፡፤በጥቅሙም ከትእምርተ መስቀል ጋር ይመሳሰላል፡፡ዮሐ 3፤14 ስለዚህ ዲያብሎስ ፈርቶ ከኛ ይርቅ ዘንድ በትእምርተ መስቀል አምሳያ እናማትባለን፡፡
፲፬.በማማተብ ቡራኬን እንቀበላለን፡፡
ዓለም በሙሉ በመርገምና በሞት ፍርድ ነበር ነገር ግን ጌታችን በመስቀል እርግማናችንን ሁሉ ተሸክሞ ከእግዚአብሔር ጋር የመታረቅ በረከትን ሰጠን ሮሜ 5፤10 በመስቀሉ የአዲስ ሕይወት በረከትና የአካሉ ክፍሎች የመሆን በረከትን ሰጠን ፡፤ከዚህም በተጨማሪ ሁሉም የአዲስ ኪዳን ጸጋዎች የተገኙት ከመስቀል ነው ፡፡ካህናትም ለመባረክ መስቀልን የሚጠቀሙት ቡራኬው ከእኛ ሳይሆን ከጌታችን መስቀል ነው ለማለት ነው፡፡በተጨማሪም ክህነታቸውን የተቀበሉት ከተሰቀለው ሊቀ ካህን ከኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ለማመልከት ነው፡፡ስለዚህ ከጌታችን የሆነውን ቡራኬ ለማግኘት በትእምረተ መስቀል አምሳያ እናማትባለን፡፡
፲፭.መሰቀል በሁሉም ምሥጢራት ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ሁሉም ምሥጢራት የተገኙት ጌታችን በመስቀል ላይ ካፈሰሰው ደሙ ነው፡፡በመስቀል ባይሆን ኖሮ በምሥጢረ ጥምቀት እግዚአብሔርን እንደ ልጁ ባልቀረብነው ነበር በመስቀል ባይሆን ኖሮ በምሥጢረ ቁርባን ሥጋውን ለመብላት ደሙን ለመጠጣት ተካፋዮች ባልሆንን ነበር በሌሎችም ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን ጸጋውን ባላገኘን ነበር፡፡ስለዚህ ጌታችን ከሰጠን ጸጋ ተካፋዮች እንሆን ዘንድ ምሥጢራቱም ይከብሩ ዘንድ አባቶቻችን ካህናት ምስጢራቱን በመስቀላቸው ሲባርኩ እኛም የምሥጢራቱ ተካፋይ ለመሆን በእምነት እንቀርባለን፡፡
፲፮ኛ.ከጌታችን ጋር ያለንን ወዳጅነት ለማስታወስ መስቀልን እbናወድሳለን፡፡
"ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ" ገላ 2፤20 "…..እርሱንና የትንሣኤውን ኃይል እንዳውቅ ከመከራውም እንድካፈል" ፊል 3፤10ያለውን የሐዋርያውን ቃል እናስታውሳለን፡፡በተጨማሪም ከጌታ ጋር የተሰቀለውን ንስሐ የገባውንና ከእርሱ ጋር በገነት ለመሆን የበቃውን ወንበዴ እናስታውሳለን፡፡ምናልባትም ያ ወንበዴ ዛሬ በገነት የቅዱስ ጳውሎስን" ከጌታ ጋር ተሰቅዬ ነበር "የሚለውን መዝሙር እየዘመረ ይሆናል፡፡የኛም ምኞት ከጌታ ጋር አብሮ መሰቀል ነው፡፡መስቀል ደግሞ ክብራችን ነው ስለዚህም ከጌታችን ጋር ያለንን ወዳጅነት ለማስታወስ በትእምርተ መስቀል አምሳያ እናማትባለን፡፡
፲፯.የአባታችን ደስታ ስለሆነ በትእምርተ መስቀል አምሳያ እናማትባለን፡፡
አብ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በመስቀል ላይ እንደሚያስደስት የኃጢአት መስዋዕትና እንደሚቃጠል መስዋዕት ተቀበለው፡፡እርሱም "የሚቃጠል መስዋዕት የእሳት ቁርባን በእግዚአብሔር ፊት ጣፋጭ ሽታ ሆነ፡ ፡" ዘሌ 1፤9 13፤17 ስለዚህም ነቢዩ ኢሳይያስ "ነፍሱን ስለ ኃጢአት መስዋዕት ካደረገ በኋላ….የእግዚአብሔር ፈቃድ በእርሱ ይከናወናል፡፡"ኢሳ 53፤10 አለ ፡፡ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድራዊ ሕይወቱ ሁሉ አብን አስደሰተ ፡፡ነገር ግን ይህንን ሁሉ በመስቀል ወደ ፍጹምነት አመጣው ፡፡"በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ ለሞትም ይኸውም ለመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ ፡፡"ፊል 2፤8 ታዲያ እኛ ክርስቶስን እስከ ሞት ድረስ በመታዘዝ እንድንመስለው እርሱ ፍጹም መታዘዝ የሚፈጸምበትን መስቀል ሁል ጊዜ እናያለን፡፡ይህም የእርሱን መታዘዝ ያስታውሰናል፡፡የጌታችን መሰቀል ለአብ እንዲሁም ለተሰቀለው ለወልድ ደስታው ነበር ፡፤ ስለዚህም ሐዋርያው" እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሶ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጧልና፡፡"ዕብ 12፡2 በማለት የጌታን ደስታ አስረዳ ፡፤ሰለዚህም የክርስቶስ የደስታው ሙላት በመስቀል ላይ ነበር፡፤እኛም ከክርስቶስ መስቀል ደስታ ተካፋዮች ያድርገን ዘንድ በትእምርተ መስቀል አምሳያ እናማትባለን ተነግሮ በማያልቅ ቸርነቱ የደስታው ተካፋዮች ያድርገን አሜን፡፡
፲፷.በመስቀል ነቀፌታውን ተሸክመን ወደ ክርስቶስ እንሔዳለን፡፡
የክርስቶስ ነቀፌታ (መከራና ስቃይ )መስቀል ነው ባማተብን ጊዜም የሕማማቱን ሣምንት እናስታውሳለን ፡፡ስለነቢዩ
"ከግብፅም ብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለጠግነት እንዲሆን አስቧልና ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራን መቀበልን መረጠ ፡፤ብድራቱን ትኩር ብሎ ተመልክቶአልና፡"ዕብ11፡26የተባለውንም እናስታውሳለን፡፡እና ነቀፌታውን ለመሸከም ወደ ክርስቶስ ለመሄድ መንገደኞች እንደሆንን ያስታውሰን ዘንድ በትእምርተ መስቀል አምሳያ እናማትባለን፡፡

፲፱ ዳግም ምጽአቱን ያስታውሰናልና በትእምርተ መስቀልአምሳያእናማትባለን፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዓለም ማለፍና ስለ ጌታችን መምጣት ሲናገር እንዲህ ይላል"በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ የታያል...."ማቴ 24፤30ይላል ታዲያ በታላቁ ምጽአቱ ጌታችን ከሰማይ ደመና ጋር ሲመጣ ለማየት የምንጠብቀው በመስቀል ላይ ሳለ የተፈፀመውን ነው"የወጉት ሁሉ ያዩታል፡፡"ራዕ 1፥6 እንዲል ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በመስቀል ላይ ሳለ በጦር የተወጋውን ምልክት ይዞ እንደሚመጣ ያስታውሰናልና የሰው ልጅ ምልክት የሆነውን መስቀል አሁን በምድር ሳለን እናከብረዋለን በትእምርተ መስቀል አምሳያ እያማተብን ትንሳኤያችንን የሀሳር ያይደለ የክብር ትንሣኤ ያደርግልን ዘንድ እንማጸንበታለንና ዛሬ በትእምርተ መስቀል እናማትባለን፡፡
ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ

Comments powered by CComment