ቤተ ክርስቲያን
-መሠረታዊ የሆነው የቤተ ክርስቲያን ትርጉም ምንድን ነው?
-መገለጫዎቿስ ምን ምን ናቸው?
ቤተ ክርስቲያን ስንል 
1.የቅዱሳን መላእክት
2.የቅዱሳን ነፍሳት
3.ሥውራን አበው
4.ተነሳሕያን ምዕመናን
የእነዚህ ሁሉ ኅብረት ናት ያለእነዚህ ኅብረት ግን ቤተ ክርስቲያን የሚባል ነገር የለም!
ቤተ ክርስቲያን የምትገለጥባቸው ጠባያቶቿ አራት ናቸው 


1.ወነአምን በአሐቲ
2.ቅድስት ቤተ ክርስቲያን
3.እንተላዕለ ኩሉ 
4.ጉባኤ ዘሐዋርያት ናት ማለትም
አንዲት ናት
ቅድስት ናት
ኩላዊት ናት
ሐዋርያዊት ናት ማለት ነው፡፡
እናስተውል 
አንዲት ናት ማለት የአንዱ የክርስቶስ አካል እንደ መሆንዋ ሁለት ሦስት ልትሆን አትችልም ራሷ ክርስቶስ አንድ ስለሆነ እሱ ራሱም "ቤተ ክርስቲያኔን እሠራታለሁ" ማቴ 16. አለ እንጂ ቤተ ክርስቲያኖቼን እሠራቸዋለሁ አላለም ስለዚህ በዓለም አቀፍ ያለች ሥሮቿ በምድር ጫፎቿ በሰማይ የሆነች 
የአማንያን ልዩ ኅብረት ናት ይችም ኅብረት ውሳጣዊ እና ምስጢራዊ አንድነት ያላት  አንዲት ናት፡፡
ቅድስት ናት ክርስቶስ በቅቡር ደሙ የቀደሳት እንደመሆንዋ መጠን ያለ ቅድስና ሊቀላቀሉባት የማይችልዋት ቅድስት ናት በአገልጋዮቿ መርከስም አትረክስም ይህማ ቢሆን ኑሮ በዓለም ተጨማልቀው የነበሩ መጥተው ንስሐ ገብተው መቀደስ አይችሉም ነበር ምክንያቱም የረከሰ አይቀድስምና ቤተክርስቲያን ግን ከሚታሰበው በላይ ቅድስት ናት፡፡
ኩላዊት ናት ይህም ማለት በሁሉ ያለች ለሁሉ የተሰጠች ዘር ቋንቋ ነገድ መልክ ቁመት ጨዋ ባርያ ሴት ወንድ የማይሉባት ላመነ ሁሉ የተሰጠች ከሁሉ በላይ የሆነች ሁሉ አንድ የሚሆኑባት የሁሉ ናት፡፡
"ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ኩላዊት ናት አስቀድማ በነቢያት በሗላም በሐዋርያት መሠረት የታነጸነች ናት አስተምህሮዋ በሁለቱ ኪዳናት ማለት በብሉይና ሐዲስ ኪዳን በትውፊት መሠረትም ላይ የጸና ነው አስተዳደርዋም ቤተ ክህነታዊ ማለትም ክህነትንና በክህነት አገልግሎት መሠረትነት ላይ የሚፈጸሙ ምስጢራትን ገንዘብ ያደረገ ነው፡፡
በመሆኑም በጳጳስ ቄስና ዲያቆን የሚመራ አስተዳደር አላት፡፡" ከአባቶች
ሐዋርያዊት ናት ይህም ማለት የመንፈሳዊ ተግባራት ሁሉ ሐዋርያችን ክርስቶስ ነው የክርስቶስ እንደመሆንዋ   ሐዋርያዊት ናት ትባላለች በሌላም የሐዋርያት ትምህርትና ባህል ትውፊትና ሥርዓት በመንፈሳዊ ሕይወት የመኖር ዘይቤው ሁሉ እንደ ሰንሰለት ሳይቋረጥ ይዛ በመገኘቷ ሐዋርያዊት ትሰኛለች፡፡
ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን የምትገለጸው በነዚህ አራቱ ነው ማለት ነው አሁን ልብ እንበል ቅድም ባልነው አንድነትም በቤተ ክርስቲያን አንድነት ውስጥ አንድ አራተኛው ብቻ ነው የሚታየው መላእክት አይታዩም ነፍሳት አይታዩም ሥውራንም ያው ሥውራን ናቸው ይህ የምስጢራውያን ኅብረት እና ውሕደት ነው ቤተ ክርስቲያን የሚባለው ቤተክርስቲያን ምስጢር ናት ማለትም ይህ ነው ምስጢር ስለተባለች ግን ምናባዊ እና ዝርው ናት ማለት አይደለም የክርስቶስ አካሉ ናት እንጂ አካለ ክርስቶስ ደግሞ ዝርው አይደለም እሱ ራሳችን እኛ ሕዋሳቶቹ የሆን የምንታይ የምንዳሰስ ምዕመናን አለን እንጂ ይችም በመላእክት ተፈጥሮ የተመሠረተች በቃል ሥግውነት አካሉ የሆነች ናት ምስጢርነቷም ይህ ነው፡፡
ልብ እንበል በተለያዩ ዘመናት የሚከሰተውን የመዋቅር ፈተና በመመልከት ልቡ የሚሸፍት አንዳንድ ሰው አለ ግን አንድ ሰው ስለቤተ ክርስቲያን ማወቅ ካለበት ከዚህ ዓለም መዋቅር ለይቶ ማየት አለበት ያለበለዚያ ግን በመዋቅሯ ውስጥ የሚያየውን ክፍተት ሁሉ የቤተ ክርስቲያን ክፍተት ነው እያለ ቤተ ክርስቲያን የአበሳ ቤት ናት ወደማለት ይደርሳል እንዲህ ካለ ደግሞ በውስጧ ለመኖር ይቸገርና ከዚህ አስደናቂ ኅብረት ይወጣል ወደሞትም ይጓዛል ማለት ነው ስለዚህ ማስተዋል ያለብን ነገር ቢኖር በደለኛ አገልጋይ ሊኖር ይችላል በደለኛ ቤተ ክርስቲያን ግን የለችም ዘረኛ አገልጋይ ሊኖር ይችላል ዘረኛ ቤተ ክርስቲያን ግን የለችም ሌባ አገልጋይ ሊኖር ይችላል ሌባ ቤተ ብርስቲያን ግን የለችም ምክንያቱም የቅዱሳን መላእክትን በገነት ያሉ የቅዱሳን ሰዎችን የሥውራንን የተነሳሕያን ምዕመናንን አንድነት ናትና፡፡
 በዚህ ዓለም ለቤተ ክርስቲያን የሚቀና የሚመስለው ግን እንደትምህርቷ መኖር ያልቻለ ለሥጋዊ ፍላጎቱ ብቻ ሲል የሚልከሰከስ አድላዊና ዘረኛ የሆነ ሰው በውሳጣዊ ውስጧ በምስጢራዊ ኅብረቷ ሊኖር አይችልም አገልጋይ ነኝ ሊል ግን ይችላል ከአንድነቷ ውጭ እንደ ሆነ ግን ግልጽ ነው፡፡
እንዲያውም አሁን አሁን ውስጥ ለውስጥ   ቤተ ክርስስቲያንን ለማጥፋት የሚፈልጉ ክፉ ሰዎች የዋሀንን ከሚያታልሉበት አንዱ ይህ የዘመኑ የአገልጋዮች የመንፈሳዊነት ክፍተትና የመዋቅሯ መላላት የካህናት ዝንጋኤና ስሁት ጉዞ ነው በዚህ ብዙ መሠረት የሌላቸው ምዕመናንን እያደናገሩ ይገኛሉ እኒህም ራሳቸውን ኢትዮጵያ የዓለም ብርሃን ራዕየ ዮሐንስ 20 ቴዎድሮስ ይመጣል ወዘተ እያሉ የሚጠሩ የጠላት ሥራ አስፈጻሚዎች ናቸው፡፡
ስለዚህ ነቅተን ራሳችንን በመጠበቅ አዲስ ነገር እንደሌለ የሚባለው  ሁሉ ትናትናም የተባለ የሚታየው ሁሉ ትናንትናም የታየ መሆኑን በመገንዘብ ከእውነት የሆነች እውነታዊት ቤተክርስቲያናችንን በምንችለው ሁሉ ማገልገል እና መሥራት ያስፈልጋል፡፡
"ኩላዊት ቤተ ክርስቲያን በዓለሙ በሙሉ የተቀበለችው እምነት አንድ ነው  ስለዚህ እውነትን ከራሳችን ቤተክርስቲያን እንጂ ከሌሎች መፈለግ አይኖርብንም" እንዳለ ሊቁ ሄሬኔዎስ
ትክክለኛው የአበው ትምህርት ይህ ነው ከዚህ ውጭ ግን ሐሰት ነው ከሷ በተቃራኒ መልኩ የሚመጡ ሁሉ የሷ ጠላቶች ናቸው እሷ እንደሆነች ያው አንዲትና ቅድስት ናት፡፡
"የክርስቶስ እጮኛ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያላደፈችና ንጽሕት ናት ድንግልና ነውርን የማታውቅ ናት የምታውቀው አንድ ነገር ነው ይህም የአንድነቷ ምስጢር መድኅን ክርስቶስ ነው፡፡ 
ይህ አንድነት በሚፈጸመው ሥርዓቷና በሥርዓቷ ውስጥ በሚታደለው ምስጢር አማካኝነት ለልጆቿ ይዳረሳል ይህንን አንድነት የማይጠብቅ ወገን የእግዚአብሔርን ሕግ መጠበቅ አይቻለውም ይህ ማለት በእውነተኛው እምነት መራመድ አይቻለውም ማለት ነው በመጨረሻም ሕይወትንም ድኅነትንም አያገኝም፡፡" እንዳለ ሊቁ ሲፕሪየን 
ይህን ሁሉ አለመረዳት በተንኮለኞች ተስበን እንድንጠፋ ያረጋልና እንጠንቀቅ
 ለዚች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች እንድንሆን ያበቁ አባቶቻችን ክብር ይገባቸዋል አሜን
አሁን ከኛ የሚጠበቀው ምንድን ነው?
1.በንጹሕ ትምህርቷ ለመኖር ያስችለን ዘንድ ከሌሎች ለይተን መሠረታዊ ትምህርቷን ማወቅ
2.የስሑታንን መልእክት ከመቀበል በመቆጠብ አንድነታችንን ማጽናት
3.ከተአምር ፍለጋ ስሜት ነጻ መሆን 
4.ልባዊና የመረዳት ሰው መሆን 
5.ከጫጫታና ግርግርታ ሕይወት መራቅ
6.ቤተ ክርስቲያንን ለነገ ሊያስተላልፍ በሚችል መልኩ መሥራት 
7.ገንዘባችን ምን ላይ መውደቅ እንዳለበት ማወቅ
8.ግለሰብን ነቢይ ነው አጥማቂ ነው ሰባኪ ነው...በማለት ተከታይ ከመሆን መጠንቀቅ
9.መዋቅርንና ቤተክርስቲያንን ለይቶ ማወቅ 
10.የሚቀያየረውን የቤተ ክርስቲያን ፈተና ተረድቶ በሁሉም ነገር ለሰማዕትነት ለመብቃት መዘጋጀት...ይህን የመሰለውን ሁሉ ያደረግን እንደሆነ በእውነት አደራ በል አንሆንም የአበው ቅዱሳን ልጆችም ነን ለመንግሥቱም እንበቃለንና እንበርታ፡፡
ስለሁሉም ነገር እግዚአብሔር ይመስገን አሜን
ተጻፈ በወለህ ነቅዐ ሕይወት 
2013ዓ.ም

Comments powered by CComment