ተወዳጆች ሆይ
እንኳን ለወለህ ነቅዐ ሕይወት ጉባኤ ቤት 3ኛ የምሥረታ በዓል በሰላም አደረሳችሁ?
ይህ ቀላል አይደለም
ሁለቱን ዓመታት እንደጸሎተ ሐሙስ ቅዳሴ በውስጥ ቢያከብርም ማለትም
1ኛውን ዓመት በደቀመዛሙርቱ ብቻ ሲያከብር 
2ኛውን ዓመት ደግሞ ከሰቆጣ እና ከአከባቢው የማኅበራትና የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ተወካዮችን እስከ ጉባኤ ቤቱ ጠርቶ ለማክበር ሞክሯል


3ኛውን ዓመት ደግሞ ጥቂት በጥቂት በማደግ በሰቆጣ ከተማ ከሰኔ አስራ ሰባት እስከ አስራ ዘጠኝ ድረስ በደብረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን  የሕዝብ ጉባኤ በማዘጋጀት የዶግማ የሥርዓት እና የትውፊት ጽንሰ አሳብ ምንድን ነው? የሚለውን ለሕዝብ ግንዛቤ በመስጠት የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡ ተኩላዎች ምዕመናንን እየጠበቀ ይገኛል፡፡
ከሀገረ ሰብከቱ ሠራተኞች እስከ ወረዳ እና እስከ አድባራት አስተዳዳሪዎች ባለሀብቶችን ጨምሮ ጠቅላላ ጉባኤ በማዘጋጀት በነገው ዕለት ማለትም (ሰኔ 19 /10/) በማኅበረ ቅዱሳን አደራሽ ጥሪ አድርጓል 
የሦስት ዓመት ጠቅለል ያለ አሳብ ይቀርባል ከተጋባዦች አስታየት ተቀብሎ ለበለጠ አገልግሎት ይዘጋጃል፡፡

🌳የሚመስለው የለም🌳
እግዚአብሔር በገናንነቱ ገናና ነው፡፡ በቅዱሳኖቹ የተቀደሰ ነው፡፡ በምስጋናውም የተመሰገነ ነው፡፡
 በክብሩም የከበረ ነው፡፡
ከመቼ ወዲህ የማይሉት ቀዳማዊ ነው፡፡ እስከ ዛሬ የማይሉት ማዕከላዊ ነው፡፡ እስከዚህ የማይሉትም ደኃራዊ ነውና ስለዚህ የሚመስለው የለም፡፡
ለአነዋዋሩ ጥንት የለውም ለአኳሗኑም ፍጻሜ የለውም ለዘመኑ ቁጥር የለውም ለዓመታቱም ልክ ቁጥር የለውምና ስለዚህ የሚመስለው የለም፡፡ ለውርዝውናው ማርጀት የለበትም፡፡ ለኃይሉም ጽናት ድካም የለበትም፡፡ ለመልኩ ጥፋት የለበትም፡፡
ለፊቱ ብርሃንም ጨለማ የለበትምና ስለዚህ የሚመስለው የለም፡፡
ለጥበቡ ባሕር ደንበር የለውም፡፡ ለትዕዛዙም ይቅርታ መስፈርት የለውም፡፡ ለመንግሥቱ ስፋት አቅም ልክ የለውም፡፡ ለአገዛዙም ስፋት ወሰን የለውምና ስለዚህ የሚመስለው የለም፡፡ 
የጥበበኞችን ምክር የሚያጠፋ ጥበበኛ ነው፡፡
የሚመክሩትን ሰዎች አሳባቸውን የሚያስረሳ አዋቂ ነው፡፡
የግብዞችን ፊት የሚያዋርድ ክቡር ነው፡፡
ባልንጀራ የሌለው አንድ ነው ዘመድ የሌለው ሥሉጥ ነው ሰማያት ይጠፋሉ የብስም ትጠፋለች ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃልእርሱ ግን እስከ ዘላለሙ እርስ ነውና የሚመስለው የለም፡፡
ሳይጠይቅ ኅሊናን ይመረምራል ሳይመረምር ልቡናን ይፈትናል ያለመብራት በጨለማ ያለውን ያያል፡፡
ጻድቁን ጽድቅ ሳይሠራ ያውቀዋል፡፡ ኃጥኡንም ኃጢአት ሳይሠራ ያውቀዋል፡፡ ልበኞቹን ከአባታቸው ወገብ ሳይወጡ ያውቃቸዋል፡፡
በደለኞችንም ከእናታቸው ማኅፀን ያውቃቸዋል፡፡
ስለዚህ የሚመስለው የለም፡፡
ለእርሱ ክብር ምስጋና ይድረሰው ለዓለመ ዓለም
ከኤጲፋንዮስ ቅዳሴ የተቀነጨበ
የሊቁ በረከት ይደርብን

 

Comments powered by CComment