የሰሙነ ሕማማት ዕለታት ስያሜና ትምህርት
ሐሙስ፡- ከስቅለትና ትንሣኤ በፊት ያለው ሐሙስ በቤተክርስቲያን ልዩ ልዩ
ስያሜዎች አሉት፡፡
፩. # ጸሎተ_ሐሙስ_ይባላል ፡- ይህ ስያሜ የተሰጠው የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ
ክርስቶስ ፍጹም መሆኑን ለማስረዳትና ለአርአያነት ጠላቶቹ መጥተው እስኪይዙት
ድረስ ሲጸልይ በማደሩ ምክንያት ነው፡፡ /ማቴ ፳፮፥፴፮-፴፯፣ ማር ፲፬፥፴፪፣ ሉቃ
፳፪፥፵-፵፮/
፪. # ሕፅበተ_ሐሙስ_ይባላል ፡- ይህ ስያሜ የተሰጠው

ጌታችን በዚህ ዕለት
የደቀመዛሙርቱን እግር በማጠቡ ምክንያት ነው፤ ይህም የሚያሳየው የዓለምን
ኃጢአት ለማጠብ የመጣ መሆኑን ነው፡፡ ይህን ለማስታወስ ዛሬም ካህናት
በተለይም ሊቃነ ጳጳሳትና የደብር አስተዳዳሪዎች፤ በመካከላችን ተገኝተህ
የእኛንና የሕዝብህን ኃጢአት አስተሥርይ ሲሉ በቤተክርስቲያን የተገኙትን
ምዕመናንን እግር በወይንና በወይራ ቅጠል ያጥባሉ፡፡ ዮሐ ፲፫፥፩-፳
፫. # የምስጢር_ቀን_ይባላል ፡- ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን አንዱ በዚህ
ዕለት ተመሥርቷልና፡፡ ይኸውም ”ይህ ስለእናንተ ነገ በመስቀል የሚፈስ ደሜ
ነው፡፡ ከእርሱም ጠጡ“ በማለት እኛ ከእርሱ ጋር፣ እርሱ ከእኛ ጋር አንድ
የምንሆንበትን መንገድ ከጠላት ዲያቢሎስ ሠውሮ፣ ለደቀመዛሙርቱ የገለጠበት
ቀን በመሆኑ የተሰጠው ስያሜ ነው፡፡ በዚህ ዕለት ቅዳሴ ይቀደሳል፣
የሚቀደሰውም በለሆሳስ ሲሆን እንደቃጭል ሆኖ የሚያገለግለውም ጸናጽል
ነው፡፡ ይህም አይሁድ ጌታችንን ለመያዝ ሲመጡ ድምፃቸውን ዝግ
አድርገው፣በለሆሳስ እየተነጋገሩ መምጣታቸውን ለማሰብ ነው፣ በቅዳሴውም
ጸሎት ተአምኆ፣ ኑዛዜ አይደረግም፣ ሥርዓተ ቁርባን ግን ይፈጸምበታል፤ ይህም
ጌታችን የሰጠውን ዘለዓለማዊ ቃልኪዳን ለማሰብ ነው፡፡ በዚህ ዕለት ክርስቲያን
የሆነ ሁሉ በንስሐ ታጥቦ ተዘጋጅቶ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን መቀበል
ይኖርበታል፡፡
፬. # የሐዲስ_ኪዳን_ሐሙስ_ይባላል ፡- ምክንያቱም መሥዋዕተ ኦሪት ማለትም
በእንስሳት ደም የሚቀርበው መሥዋዕት ማብቃቱን ገልጦ፣ ለድኅነተ ዓለም
ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበበት ዕለት በመሆኑ ነው፡፡ “ይህ ጽዋዕ
ስለ እናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው ከእርሱም ጠጡ”
በማለቱ ይታወቃል /ሉቃ ፳፪፥፳/
ኪዳን ማለት በሁለት ወገን መካከል የሚደረግ ውል፣ ስምምነት፣ መሐላ ማለት
ነው፡፡ በዚህ መሠረት ጌታችን ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ዘለዓለማዊ ቃልኪዳን
በራሱ ደም የፈጸመበት ዕለት መሆኑን በማሰብ የቃል ኪዳኑ ፈጻሚዎች፣
ጠባቂዎች መሆን እንደሚገባን እንማራለን፡፡
፭. # የነፃነት_ሐሙስ_ይባላል ፡- ለኃጢአትና ለዲያቢሎስ ባሪያ ሆኖ መኖር
ማብቃቱ፣ የሰው ልጅ ያጣውን ክብር መልሶ ማግኘቱ የተረጋገጠበት ቀን ስለሆነ
ነው፡፡ ራሱ ጌታችን ስለሰው ልጅ ነፃነት ሲናገር ”ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች
አልላችሁም ባሪያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና ወዳጆች ግን ብያችኋለህ“
በማለቱ /ዮሐ ፲፭፥፲፭/ ከባርነት የወጣንበት ቀን መሆኑን መጽሐፉ በግልጥ
ያስረዳናል፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ ክርስቲያን ከኃጢአት ባርነት ርቆ፣
ከእግዚአብሔር ጋር የሚያወዳጀውን መልካም ሥራ በመሥራት ሕይወቱን
መምራት ይኖርበታል፡፡ እርሱ ጠላቶቹ ስንሆን ወዳጆቹ አድርጎናልና፡፡
በዚህ ዕለት በወንጌላት የተመዘገቡ ድርጊቶችን ቀጥለን እንመለከት
፩. # የፋሲካ_ዝግጅት_የተደረገበት_ዕለት_ነው ፡- ዝግጅቱም በሦስት ወንጌላት
ላይ ተመዝግቧል / ማቴ ፳፮፥፲፯-፲፱፣ ማር ፱፱፬፥፲፪-፲፮፣ ሉቃ ፳፪፥፯-፲፫/ፋሲካ
ማለት ማለፍ ማለት ነው፤ ይኸውም እስራኤላውያን በግብፅ ምድር ሳሉ
መልአኩን ልኮ እያንዳንዱ እሥራኤላዊ የበግ ጠቦት እንዲያርድና ደሙን
በማበሉበት ቤት ሁለቱን መቃንና ጉበኑን እንዲቀባ ለሙሴ ነገረው፣ ሙሴም
ለሕዝቡ ነገረ፣ ሁሉም እንደታዘዙት ፈጸሙ፡፡ መቅሠፍት ከእግዚአብሔር ታዞ
መልአኩ የደም ምልክት የሌለበትን የግብፃውያንን ቤት በሞተ በኩር ሲመታ፣
የበጉ ደም ምልክት ያለበትን የእሥራኤላውያንን ቤት ምልክቱን እያየ ማለፉን
ለማመልከት ነው /ዘጸ ፲፪፥፩-፲፫/ በዚህ መነሻነት በየዓመቱ እስራኤላውያን
በመጀመሪያ ወራቸው በ፲፱ኛው ቀን በግ እያረዱ የፋሲካን በዓል ያከብራሉ፡፡
ሀገራችንም አስቀድሞ ብሉይ ኪዳንን የተቀበለች አገር እንደመሆኗ ይህ ድርጊት
ይፈጸምባት ነበር፡፡ በአንጻሩም ዛሬ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ፋሲካ
ተብሎ የተጠራበት ምክንያት በዚህ በፋሲካ በዓል ራሱን የተወደደ መሥዋዕት
አድርጎ ደሙን ስላፈሰሰልን ነው፡፡ በደሙ መፍሰስ ሞተ በኩር የተባለ ሞተ ነፍስ
ቀርቶልናልና፡፡ “ፋሲካችን ክርስቶስ ነው” /፩ኛ ቆሮ ፭፥፯፣ ፩ ጴጥ ፩፥፲፰-፲፱ /
፪. # በዚህ_ዕለት_እንደማክሰኞ_ለደቀመዛሙርቱ_ረጅም_ት
ምህርት_አስተምሯል ፡፡ /ዮሐ ፲፱፥፲፮/ የመጽሐፍ ክፍል የሚገኘው በጠቅላላ
የዚህ ዕለት ትምህርት ነው፡፡ የትምህርቱም ዋና ዋና ክፍሎች ምሥጢረ ሥላሴ /
የሦስትነት ትምህርት/ ምሥጢረ ሥጋዌ/ የአምላክ ሰው መሆን ምሥጢረ
ትንሣኤ ሙታንና /የዳግም ምጽአቱ ነገር ነው/ እነዚህን በስፋትና በጥልቀት
መማር እንደሚገባን ሲያስረዳን፣ በተአምራት ሊገልጥላቸው ሲችል በረጅም
ትምህርት እንዲረዱት አድርጓል፡፡ ተማሪዎቹም እሱ እያስተማራቸው ሳለ
ያልገባቸውንም እየጠየቁ ተረድተዋል፡፡ ከዚህም እያንዳንዳችን በቤተክርስቲያን
ተገኝተን መማርና ያልገባንን ጠይቀን መረዳት እንደሚገባን እናማራለን፡፡
፫. # ከደቀመዛሙርቱ_አንዱ_የአስቆሮቱ_ይሁዳ_የተባለው_
ጌታ_ሆይ_መምህር_ሆይ_ብሎ_በመሳም_አሳልፎ_ጌታው
ን_የሰጠበት_ዕለት_ነው ፡፡ ጭፍሮቹም በዚሁ ዕለት ሌሊት የክብር ባለቤት
የሆነው ጌታችንን ይዘው ወደፊት ወደኋላ እየጎተቱ፣ እያዳፉ ወደ ሊቀ ካህናቱ
ወደ ቀያፋ ወስደውታል፡፡ /ማቴ ፳፮፥፵፯-፶፰/
ምንጭ፡- መለከት መጽሔት ፳፻፯ ዓ.ም

Comments powered by CComment