ክርስቶስ፡ የኹሉ፡ ጌታ 


የዘመናችን፡ መናፍቃን፡ እንደሚያስተምሩት፣ በውኑ፡ ጌታችን፡ ኢየሱስ፡ ክርስቶስ፡ አማላጅ ወይም፡ ማላጅ ነውን? 

<<ሎቱ፡ ስብሐት>>፡ ምስጋና፡ ይግባውና፣ ጌታችን፡ ኢየሱስ፡ ክርስቶስ፡ አምላክ፡ ወልደ፡ አምላክ፡ ስለሆነ፣ ተማላጅ፣ ተለማኝ፣ አዳኝ፣ ይቅር፡ ባይ፡ ነው፡ እንጂ፡ ርሱን፡ እንደ፡ ፍጡር፡ አማላጅ፡ ነው፡ ማለት፡ ታላቅ፡ ክህደት፡ ነው።
ክርስቶስ፡ ተማላጅና፡ አዳኝ፡ አምላክ፡ መሆኑን፡ መጽሐፍ፡ ቅዱስ፡ በየምእራፉ፡ ያረጋግጣል። ለመረዳትም፡ ያህል፡ ከብዙ፡ በጥቂቱ፡ ቀጥለን፡ እንመልከት፦

፩ኛ. ነብዩ፡ ኢሳይያስ፡ ኢየሱስ፡ ክርስቶስ፡ ተለማኝ፣ ተማለጅ፡ አምላክ፡ መሆኑን፡ አስረድቶአል።

<<ሕፃን፡ ተወልደ፡ ለነ፣ ወልድ፡ ተውኅበ ለነ፣ ወቅድመት፡ (ወሥልጣን)፡ ኮነ፡ ዲበ፡ መትከፍቱ። ወይሰመይ፡ ስሙ፡ አቢየ፡ ምክር፣ አበ፡ ዓለም፣ ወመልአከ፡ ሰላም>>፣
-ሕፃን፡ ተወልዶልናል፤ ወንድ፡ ልጅም፡ ተሰጥቶናል፣ መንግስትም፡ በጫንቃው፡ ኾነ፤ ስሙም፡ አቢየ፡ ምክር፣ አበ፡ ዓለም፣ ንጉሠ፡ ሰላም፡ ይባላል>>፡ ሲል፡ መስክሮአል።
(ትንቢተ፡ ኢሳይያስ፡ ግእዝና፡ አማርኛ፡ ዘማኅበረ፡ ሐዋርያት፡ (ምእ.፱፥፮)።  ብርሃንና፡ ሰላም፡ በታተመው፡ የአማርኛ፡ መጽሐፍ፡ ቅዱስ፡ ደግሞ፡ በበለጠ፡ ግልጽ፡ ኾኖ፡ ይነበባል፦ <<ሕፃን፡ ተወልዶልናልና፣ ወንድ፡ ልጅም፡ ተሰጥቶናልና፣ አለቅነትም፡ በጫንቃው፡ ላይ፡ ይሆናል፤ ስሙም፡ ድንቅ፡ መካር፣ ኀያል፡ አምላክ፣ የዘለዓለም፣ የሰላም፡ አለቃ፡ ተብሎ፡ ይጠራል>> ይለዋል፡ (ኢሳ.፱፥፮)።


፪ኛ. ነብዪ፡ ዳንኤልም፡ ክርስቶስ፡ ለዘለዓለማዊ፡ ንጉስ፣ የማያልፍ፡ ጌታ፡ መኾኑን፡ ሲመሰክር፡ እንዲህ፡ ብሎአል።

<<መናብርትም፡ (ዙፋኖችም)፡ ሲዘረጉ፡ አየሁ፤ በዘመናት፡ የሸመገለ፡ (ለዘለዓለም፡ የኖረ)፡ በዙፋኑ፡ ላይ፡ ተቀመጠ፤ ልብሱም፡ እንደ፡ በረዶ፡ ነጭ፤ የራሱም፡ ጠጉር፡ እንደ፡ ጥሩ፡ ጥጥ፡ ነበረ፣ መንኰራኩሮቹም፡ (ሰረገሎቹም)፡ የሚነዱ፡ እሳት፡ (ነበልባለ፡ እሳት)፡ ነበሩ። የእሳት፡ ፈሳሽ፡ (ፈለገ፡ እሳት)፡ ከፊቱ፡ ይፈልቅና፡ ይወጣም፡ ነበረ፣ ሺህ፡ ጊዜ፡ ሺህ፡ (አእላፈ፡ አእላፋት)፡ ያገለግሉት፡ ነበረ፣ እልፍ፡ አእላፋትም፡ በፊቱ፡ ቆመው፡ ነበረ። ፍርድም፡ ኾነ፣ መጻሕፍትም፡ ተገለጡ…>>በማለት፡ ኢየሱስ፡ ክርስቶስ፡
ፈራጅ፡ አምላክ፣ የማያልፍ፡ ንጉሥ፡ መኾኑን፡ ነብዩ፡ መስክሮአል፡(ዳን.፯፥፱-፲፩)።


፫ኛ. ቅዱስ፡ ዮሐንስም፡ እንደ፡ ነቢዩ፡ ዳንኤል፡ ስለ፡ ክርስቶስ፡ አምላክነት፡ ሲመሰክር፡ እንዲህ፡ ብሎአል። <<የሚናገረኝንም፡ ድምፅ፡ ለማየት፡ ዘወር፡ አልሁ፤ ዘወር፡ ብየም፡ ሰባት፡ የወርቅ፡ መቅረዞች፡ አየሁ፤ በመቀረዞቹም፡ መካከል፡ የሰው፡ ልጅ፡ የሚመስለውን፡ አየሁ፤ ርሱም፡ እስከ፡ እግሩ፡ ድረስ፡ ልበስ፡ የለበሰ፣ ደረቱም፡ በወርቅ፡ መታጠቂያ፡ የታጠቀ፡ ነበር። ራሱና፡ የራሱ፡ ጠጕርም፡ እንደ፡ ነጭ፡ የበግ፡ ጠጕርና፡ እንደ፡ በረዶም፡ ነጭ፡ ነበሩ፤ ዓይኖቹም፡ እንደ፡ እሳት፡ ነበልባል፡ ነበሩ፤ እግሮቹም፡ በእቶን፡ የነጠረ፡ የጋለ፡ ናስ፡ይመስሉ፡ ነበር፣ ድምፁም፡ እንደ፡ ብዙ፡ ውኃዎች፡ ድመፅ፡ ነበር፣ በቀኝ፡ እጁም፡ ሰባት፡ ከዋክብት፡ ነበሩት፤ ከአፉም፡ በኹለት፡ ወገን፡ የተሳለ፡ እጅግ፡ ስለታም፡ ሰይፍ፡ ወጣ፤ ፊቱም፡ በኃይል፡ እንደሚያበራ፡ እንደ፡ ፀሐይ፡ ነበረ>> በማለት፡ ቅዱስ፡ ዮሐንስ፡ መስክሮአል፡ (ራእ.፩፥፲፪-፲፮)።


ጌታችን፡ ኢየሱስ፡ ክርስቶስ፡ ለአገላጋዮ፡ ለዮሐንስ፡ በማጽናኛ፡ ቃል፡ እንዲህ፡ አለው፦
<<አትፍራ፣ ፊተኛውና፡ መጨረሻው፡ ሕያውም፡ እኔ፡ ነኝ፤ ሞቼ፡ ነበርሁ፤ አሁንም፡ ከዘለዓለም፡ እስክ፡ ዘለዓለም፡ ድረስ፡ ሕያው፡ ነኝ፤ የሞትና፡ የሲኦል፡ መክፈቻ፡ አለኝ>>፡ (ራእ.፩፥፲፯-፲፱)።

እንዲህ፡ ያለውን፡ ጌታ፡ ነው፡ መናፍቃን፡ አማለጅ፡ የሚሉት? 


አዎን፡ ለኃጢአት፡ ደፋሮች፡ ናቸውና፣ ሞትንና፡ ሲኦልን፡ ያሸነፈውን፣ እልፍ፡ አእላፋት፡ መላእክት፡ በፊቱ፡ በመቆም፡ የሚያመሰግኑትን፡ ጌታ፡ ጌትነቱን፣ ፈራጅነቱን፣ አምላክነቱን፡ በመካድ፡ አማላጅ፡ ይሉታል። ምስጋና፡ ይግባውና፡ ይቅር፡ ይበላቸው።

፬ኛ. ቅዱስ፡ ዮሐንስ፡ ሲመሰክር፣ <<አብ፡ ልጁን፡ ይወዳል፣ ኹሉንም፡ በእጁ፡ ሰጥቶታል፣ በልጁ፡ (በወልድ)፡ የማያምን፡ ግን፡ የእግዚአብሔር፡ ቁጣ፡ (ፍርድ)፡ በርሱ፡ ይኖራል፡ እንጂ፡ ሕይወትን፡ አያይም>>፡ ብሎአል፡ (ዮሐ.፫፥፴፭-፴፮)። ስለዚህ፡ ኹሉ፡ በእጁ፡ የኾነውን፡ ጌታ፡ መሐሪ፣ አዳኝና፡ ተማላጅ፡ መሆኑን፡ ማመን፡ ይገባል፤ እሱንም፡ በማመን፡ ዘለዓለማዊ፡ ሕይወትን፡ መውረስ፡ ተገቢ፡ ነው። ነገር፡ ግን፡ ኢየሱስ፡ ክርስቶስ፡ ተማላጅ፡ አዳኝ፣ ይቅር፡ ባይ፡ መሆኑን፡ በመካድ፡ እሱን፡ <<አማላጅ፣ ጠበቃ>>፡ ነው፡ ብሎ፡ የሚያምን፡ ኹሉ፡ ይፈረድበታል፡ (ዮሐ.፫፥፲፰)።


፭ኟ. የነበሩባት፡ መርከብ፡ በማእበል፡ ልትገለበጥባቸው፡ በተንገዳገደች፡ ጊዜ፡ ደቀ፡ መዛሙርቱ፡ በሙሉ፡ ወደ፡ ጌታ፡ ቀርበው፡ <<ጌታ፡ ሆይ፡ አድነን፣ ጠፋን>>፡ እያሉ፡ ለመኑት። እሱም፡ ልመናቸውን፡ ሰምቶ፡ ነፋሱንና፡ ማእበሉን፡ ገሠጸ፤ ታላቅ፡ ጸጥታም፡ ኾነ፡ (ማቴ.፰፥፳፭-፳፯)። ነፋሱንና፡ ማእበሉን፡ በቃሉ፡ በመገሠጹና፡ በማዘዝ፡ ባሕሩንም፡ ጸጥ፡ አድርጎ፡ ደቀ፡ መዛሙርቱን፡ ያዳነ፡ ኃያል፡ ጌታን፡ በኃጢአት፡ የሰከሩ፡ ሰዎች፡ በሰማይ፡ ኾኖ፡ ያማልዳል፡ ይሉታል፤ ሎቱ፡ ስብሐት።


፮ኛ. በሌላ፡ ጊዜ፡ ደግሞ፡ አንድ፡ ሰው፡ ወደ፡ ርሱ፡ ቀረበና፡ ተንበርክኮ፡ <<ጌታ፡ ሆይ፡ ልጄን፡ ማርልኝ፣ በጨረቃ፡ እየተነሳበት፡ ክፉኛ፡ ይሠቃያልን፣ ብዙ፡ ጊዜም፡ በእሳት፡ ላይ፡፣ ብዙ፡ ጊዜም፡ በውኃ፡ ላይ፡ ይወድቃል፣ ወደ፡ ደቀ፡ መዛሙርትህም፡ አመጣሁት፣ ሊፈውሱት፡ አልቻሉም>>፡ አለው። ኢየሱስም፡ መልሶ፦ <<የማታምን፡ ጠማማ፡ ትውልድ፡ ሆይ፣ እስከ፡ መቼ፡ ከእናንተ፡ ጋር፡ እኖራለሁ? እስከ፡ መቼ፡ እታገሳችኋለሁ? ወደዚህ፡ ወደ፡ እኔ፡ አምጡት>>፡ አለ። ኢየሱስም፡ ጋኔኑን፡ ገሠጸው፡ ጋኔኑም፡ ከበሽተኛው፡ ወጣ፤ ብላቴናውም፡ ከዚያች፡ ሰዓት፡ ጀምሮ፡ ተፈወሰ፡ (ማቴ.፲፯፥፲፬-፲፱)።


፯ኛ. በቅፍርናሆም፡ ከተማ፡ ጌታችን፡ በምኩራብ፡ ሲያስተምራቸው፡ ሳለ፡ አንድ፡ ርኩስ፡ መንፈስ፡ ያደረበት፡ ሰው፡ በዚያ፡ ነበር፤ በታላቅ፡ ድምጽም፡ ጮኽ፦ <<ተው፡ የናዝሬቱ፡ ኢየሱስ፡ ሆይ፣ ካንተ፡ ጋር፡ ምን፡ አለን? ልታጠፉን፡ አለ። ኢየሱስም፦ <<ዝም፡ በል፣ ከእርሱም፡ ውጣ>>፡ ብሎ፡ ገሠጸው። ጋኔኑምከእርሱ ወጣ። ሁሉንም መደነቅ ያዛቸው፣ እርስ፡ በርሳቸውም፦ <<ይህ፡ ቃል፡ ምንድን፡ ነው? በሥልጣንና፡ በኃይል፡ ርኩሳን፡ መናፍስትን፡ ያዝዛል፣ እነሱም፡ ይወጣሉ>>፡ ብለው፡ ተነጋገሩ፡ (ሉቃ.፬፥፴፭-፴፯)።

ከዚህ፡ በላይ፡ እንደተመለከትነው፣ ጌታችን፡ ኢየሱስ፡ ክርስቶስ፡ ሞትን፡ አሸንፎ፡  ሙታንን፡ የሚያነሣ፣ በአጋንንት፡ ከተያዙት፡ ሕሙማን፡ አጋንንትን፡ በቃል፡  እያዘዘና፡ እየገሠጸ፡ የሚፈውስ፡ ጌታ፡ መሆኑን፡ ወንጌላውያኑ፡ እያረጋገጡና፡  እያስረዱ፣ ገልጸው፡ እያስተማሩን፣ እንዴት፡ አማለጅ፡ ይባላል? ርሱ፡ አማለጅ፡ ከተባለ፡ ተማላጅ፡ ማን፡ ሊሆን፡ ነው? ሕሙማንን፡ (በሽተኞችን)፡ ሲፈውስ፣ አጋንንትን፡ ከበሽተኞች፡ ሲያወጣ፡ ማንን፡ ለምኖ፡ ያውቃል? <<እነዚህ፡ በሽተኞች፡ ፈውሳቸው፣ ይህችን፡ የሞተች፡ ልጅ፡ አድንልኝ>>፡ ብሎ፡ የለመነበት፡ ጊዜ፡ ነበርን? ለርሱ፡ ምስጋና፡ ይግባውና፡ አንድም፡ ጊዜ፡ አላደረገውም፣ ወንጌላውያኑም፡ አልነገሩንም፣ የቀሩት፡ ሐዋርያትም፡ አላስተማሩንም። ምክንያቱም፡ ራሱ፡ አዳኝና፡ ይቅር፡ ባይ፡ አምላክ፡ ነውና፤ መሐሪም፡ ነውና።


፰ኛ. ኢየሱስ፡ ክርስቶስ፡ አምላክ፡ ነው። ስለዚህ፡ ተማላጅና፡ አዳኝ፡ ነው፡ እንጂ፡ አማላጅ፡ አይደለም። ሐዋርያትም፡ እዲህ፡ ብለው፡ አስተምረዋል። ሐዋሪያው፡ ቅዱስ፡ ጳውሎስ፡ ሲመሰክር፦ <<ወእሙንት፡ አበዊነ፡ ወእምላእሌሆሙ፡ ተወልደ፡ ክርስቶስ፡ በሥጋ፡ ሰብእ፡ዘውእቱ፡ አምላክ፡ ቡሩክ>>፤ <<እነርሱ፡ አባቶቻችን፡ ናቸውና፣ ከእነርሱም፡ ክርስቶስ፡ በሥጋ፡ ተወለደ፣ (መጣ)፣ እርሱም፡ ከኹሉ፡ በላይ፡ የኾነ፡ ቡሩክ፡ አምላክ፡ ነው>>፡ ብሎአል፡ (ሮሜ.፱፥፭)። ከዚሁም፡ አክሎ፡ ሲያስተምር፡ እንዲህ፡ ብሎአል፡ <<ሰዎችን፡ ኹሉ፡ የሚያድን፡ የእግዚአብሔር፡ ጸጋ፡ ተገልጦአል፣ ይህም፡ ጸጋ፡ ኃጢያትንና፡ ዓለማዊን፡ ምኞት፡ ከደነ፡ የተባረከውን፡ ተስፋችንን፣ ርሱም፡ የታላቁን፡ የአምላክችንንና፡ የመድኃኒታችንን፡ የኢየሱስ፡ ክርስቶስን፡ ክብር፡ መገለጥ፡ እየተጠባበቅን፡ (እየጠበቅን)፡ ራሳችንን፡ በመግዛትና፡ በጽድቅ፡ እግዚአብሔርን፡ በመምሰል፡ በአሁኑ፡ ዘመን፡ እንድንኖር፡ ያስተምረናል>>፡ (ቲቶ. ፪፥፲፩-፲፬)።

ራሱ፡ ጌታችን፡ መድኃኒታችን፡ እየሱስ፡ ክርስቶስንም፡ ሲያስተምር፡ <<በመንፈስ፡ ቅዱስ፡ ላይ፡ የስድብ፡ ቃል፡ የሚናገር፡ ኹሉ፡ በዚህ፡ ዓለምም፡ ቢኾን፣ ወይም፡ በሚመጣው፡ ዓለም፡ ኃጢአቱ፡ አይሰረይለትም>> ብሎአል፡ (ማቴ. ፲፪፥፴፩-፴፪)። ስለዚህ፡ የኢየሱስ፡ ክርስቶስን፡ አምላክነትን፣ አዳኝነቱን፣ ተማላጅነቱንና፡ ይቅር፡ ባይነቱን፡ በመካድ፡ ወደ፡ ሰማይ፡ ካረገ፡ በኋላ፡ በዚያ፡ ኾኖ፡ ያማልዳል፣ ይጸልያል፡ የሚሉት፡ ኹሉ፡ ምን፡ ጊዜም፡ ኃጢአታቸው፡ አይሰረይላቸውም።

፱ኛ. ሐዋርያው፡ ቅዱስ፡ ጻውሎስ፡ ኢየሱስ፡ ክርስቶስ፡ የማይሻር፡ ንጉሥና፡ የማይለወጥ፡ የዘለዓለም፡ አምላክ፡ መኾኑን፡ እየመሰከረ፡ ምስጋና፡ ያቀርብለታል፣ እንዲህ፡ እያለ፦
<<ወውእቱ፡ ንጉሥ፡ ዘለዓለም፡ ዘኢይመውት፡ ወዘእያስተርእ፡ አምላክ፣ ሎቱ፡ ክብር፡ ወስብሐት፡ ለዓለመ፡ ዓለም>>፡ እያለ፡ አመስግኖአል። ማለት፦ <<ብቻውን፡ አምላክ፡
ለሚኾን፣ ለማይጠፋው፣ ለማይለወጠው፣ ለማይታየው፡ ለዘመናት፡ ንጉሥ፡ ምስጋናና፡ ክብር፡ እስከ፡ ዘለዓለም፡ ድረስ፡ ይኹን>>፡ እያለ፡ ያመሰገነው፡ ጌታ፡ ፈራጅ፣ መሐሪ፣ ተለማኝና ይቅር፡ ባይ፡ አምላክ፡ መኾኑን፡ በመረዳት፡ ነው። የአንድ፡ አገር፡ ንጉሥ፡ በግዛቱ፡ (በአገሩ)፡ ፈራጅ፣ አዛዥ፣ መሐሪና፡ ቀጪ፡ እየኾነ፡ ሕዝቡን፡ ይመራል፡ እንጂ፣ አማላጅ፡ እንደማይኾን፡ ኹሉ፣ ኢየሱስ፡ ክርስቶስም፡ ሕልፈትና፡ ፍጻሜ፡ በሌለው፡ በመንግስቱ፡ ይፈርዳል፣ ይምራል፣ ይቀጣል፡ እንጂ፡ ያማልዳል፡ ተብሎ፡ ሊነገርለት፡ ከቶ፡ አይገባም።


፲ኛ. በእርግጥ፡ አምላክ፡ ወልደ፡ አምላክ፡ የኾነው፡ ክርስቶስ፡ ሥጋ፡ በመልበሱና፡ ከኃጢአት፡ በቀር፡ ፍጹም፡ ሰው፡ በመኾኑ፡ <<ወልደ፡ እጓለ፡ እመሕያው>>፡ ማለት፡ የሰው፡ ልጅ፣ የዳዊት፡ ልጅ፣ ተብሎ፡ ተጠርቶአል። በዚሁ፡ ምሥጢር፡ ርሱ፡ ራሱ፡ ለአሥራ፡ ኹለቱ፡ ደቀ፡ መዛሙርት፡ ሲነግራቸው፦ <<እነሆ፡ ወደ፡ ኢየሩደሳሌም፡ እንወጣለን፣ የሰው፡ ልጅም፡ ለካህናት፡ አለቆችና፡ ለጻፎች፡ አልፎ፡ ይሰጣል፣ የሞት፡ ፍርድም፡ ይፈረዱበታል፣ ሊዘባበቱበትም፣ ሊገርፉትም፣ ሊሰቅሉትም፡ ለአሕዛብ፡ አሳልፈው፡ ይሰጡታል፤ ይሰቅሉታልም፤ በሦስተኛውም፡ ቀን፡ ይነሣል>>፡ አላቸው፡ (ማቴ.፳፥፲፯-፲፱)። በዚሁ፡ መሠረት፡ ኢየሱስ፡ ክርስቶስ፡ ለእኛ፡ አርአያ፡ ለመኾን፡ በመከራ፡ ጊዜና፡ በፈተና፡ ጊዜ፡ መጸለይ፡ እንደሚገባን፡ ለማስተማር፡ በለበሰው፡ ሥጋ፡ ማለት፡ በሰውነቱ፡ በጌቴ፡ሴማኒ፡ ጸልዮአል፡ (ማቴ.፳፮፥፴፮-፵፮)። እንደዚሁም፡ የሰውነት፡ ወዙ፡ ወደ፡ ምድር፡ እስኪንጠባጠብ፡ ድረስ፡ በምድር፡ እየሰገደ፡ መጸለዩ፡ የታመነ፡ ነው፡ (ሉቃ.፳፪፥፴፱-፵፮)። በተጨማሪም፡ ጌታችን፡ ኢየሱስ፡ ክርስቶስ፡ ለእኛ፡ ምሳሌውን፡ ለመስጠትና፡ አማናዊ፡ ትስብእትን፡ (ሰውነትን)፡ እንደ፡ ተዋሐደ፡ ለማስረዳት፣ <<አሁንስ፡ ነፍሴ፡ ታውካለች፣ ምን፡ እላለሁ፣ አባት፡ ሆይ፡ ከዚች፡ ሰዓት፡ አድነኝ>>፡ ብሎ፡ ጸለየ፡ (ዮሐ.፲፪፥፳፯)። ይህንን፡ በጌቴሰማኒ፡ የጸለየው፡ ጸሎት፡ (ሉቃ.፳፪፥፵፫-፵፭)፡ በማሰብ፡ ሐዋርያው፡ ቅዱስ፡ ጳውሎስ፡ ለእብራውያን፡ ክርስቲያኖች፡ በጻፈው፡ መልእክቱ፡ <<ርሱም፡ (ክርስቶስ)፡ በሥጋው፡ ወራት፡ (በሰውነቱ፡ ወራት)፡ ከሞት፡ ሊያድነው፡ ወደሚችል፡ ከብርቱ፡ ጩኸትና፡ እንባ፡ ጋር፡ ጸሎትንና፡ ምልጃን፡ አቀረበ>>፡ ብሎ፡ ጻፈላቸው፡ (እብ.፭፥፯)። ይኸውም፡ እግዚአብሔርንና፡ ሰውን፡ ለማስታረቅ፡ ራሱ፡ እግዚአብሔር፡ እየሱስ፡ ክርስቶስ፡ በሰውነቱ፡ (በለበሰው፡ ሥጋ)፡ ሊቀ፡ ካህናት፡ ኾኖ፡ መገለጡንና፡ የማስታረቅ፡ አገልግሎት፡ መፈጸሙን፡ ያመለክታል።

፲፩ኛ. እየሱስ፡ ክርስቶስ፡ ሊቀ፡ ካህናት። በዘመነ፡ ኦሪት፡ በኦሪቱ፡ ሕግ፡ መሠረት፡ በየጊዜው፡ የተሾሙት፡ ካህናት፡ (ሊቃን፡ ካህናት)፡ ሕጉ፡ በሚያዘው፡ መሠረት፡ ስለ፡ ሕዝቡ፡ኃጢአትና፡ በደል፡ መሥዋእት፡ ያደርጉ፡ ነበር፤ መሥዋእቱንም፡ በማቅረብና፡ በማሳረግ፡ የተሠውትንም፡ እንስሳት፡ ደም፡ በመርጨት፡ የተሾመው፡ ካህን፡ ኃጢአትን፡ ያስተሰርይ፡
ነበር፡ (ዘሌዋ.፬፥፴፭፤ ፭፥፮፤ ፮፥፭-፯)።


እንደዚሁም፡ እየሱስ፡ ክርስቶስ፡ የሰውን፡ ልጆች፡ ከበደልና፡ ከኃጢአት፡ ያነጻ፡ ዘንድ፡ (ይቅር፡ ይል፡ ዘንድ)፡ ካህን፣ ሊቀ፡ ካህናት፡ ኾነ። (ወክርስቶስኒ፡ ከዊኖ፡ ሊቀ፡ ካህናት፡ ለእንተ፡ ትመጽእ፡ ሠናይት፡ በውስተ፡ እንተ፡ ተአቢ፡ ወትሔይስ፡ ደብተራ፣ እንተ፡ እገብራ፡ እደ፡ ሰብእ፣ ወእኮነት፡ በውስተዝ፡ ዓለም>> ፡ በማለት፡ ሐዋርያው፡ አስተምሮአል። <<ክርስቶስ፡ ይመጣ፡ ዘንድ፡ ላለው፡ መልካም፡ ነገር፡ ሊቀ፡ ካህናት፡ ኾኖ፣ በምትበልጠውና፡ በምትሻለው፡ በሰው፡ እጅም፡ ባልተሠራች፡ በዚህ፡ ዓለም፡ ባልኾነች፡ ድንኳን፡ ዘላለማዊ፡ ቤዛ፡ ኾኖ፡ ገባ…>>፡ በማለት፡ ሐዋርያው፡ ቅዱስ፡ ጳውሎስ፡ ጽፎአል፡ (እብ.፱፥፲፩-፲፬)።

በሌላው፡ ቦታም፡ ሐዋርያው፡ ሲያስረዳ፡ <<ወብነ፡ ሊቀ፡ ካህናት፡ እየሱስ፡ ክርስቶስ፡ ወልደ፡ እግዚአብሔር፡ ዘተለአለ፡ እምሰማያት፣ ወበእንተዝ፡ ናጽንእ፡ እንከ፡ አሚነ፡ ቦቱ>>፦ <<ከሰማያት፡ ከፍ፡ ከፍ፡ ያለ፡ ወልደ፡ እግዚአብሔር፡ እየሱስ፡ ክርስቶስ፡ ሊቀ፡ ካህናት፡ አለን፣ ስለዚህም፡ በርሱ፡ ማመንን፡ እናጽና>>፡ ብሎአል፡ (እብ.፬፥፲፬)። እንደገናም፡ ይኽ፡ ቅዱስ፡ ሐዋርያ፡ ስለዚህ፡ ሲያስተምር፡ <<ዘክመዝኬ፡ ሊቀ፡ ካህናት፡ ይደልወነ፡ ጻድቅ፡ ወየዋህ፣ ንጸሕ፡ ወርሑቅ፡ እምኵሉ፡ ኃጢአት፣ ወልUል፡ እምሰማያት>>፡ ብሎአል። ማለትም፡ <<ቅዱስና፡ ተንኮል፡ የሌለበት፣ ከኃጢአትም፡ ፈጽሞ፡ የተለየ፡ (ንጹሕ፡ የኾነ)፣ ከሰማያት፡ ከፍ፡ ከፍ፡ ያለ፣ እንደዚህ፡ ያለ፡ ሊቀ፡ ካህናት፡ ይገባናል…>>፡ በማለት፡ አስተምሮአል፡ (እብ.፯፥፳፮)።

ስለዚህ፡ ወልደ፡ እግዚአብሔር፡ ክርስቶስ፡ በሥጋዌው፡ ወራት፡ (በሰውነቱ፡ ወራት)፡ በነሣው፡ ማለት፡ በተዋሐደው፡ ሥጋ፡ ሊቀ፡ ካህናት፡ ኾኖ፡ በመገለጡ፣ <<አሐዱ፡ ኀሩይ፡ ማእከለ፡ እግዚአብሔር፡ ወሰብ>>፡ <<በእግዚአብሔርና፡ በሰው፡ መካከል፡ የተመረጠ፡ ኾነ…>>፡ ተባለ፡ (፩ጢሞ.፪፥፭)። <<ወበእንተዝ፡ ለሐዲስ፡ ሥርአት፡ እየሱስ፡ ኅሩየ፡ ኮነ>>፦ <<ስለዚህ፡ ለአዲሲቱ፡ ሥርአት፡ (ሐዲስ፡ ኪዳን)፡ እየሱስ፡ የተመረጠ፡ ኾነ…>>፡ ተብሎ፡ ተነገረለት፣ ተጻፈለት፡ (እብ.፱፥፲፭)።

በዚሁ፡ ሊቀ፡ ካህናት፡ ኾኖ፡ በተገለጠበት፡ አገልግሎት፡ እየሱስ፡ ክርስቶስ፡ <<ወአንሰ፡ በእንቲአሆሙ፡ እስእል>>፣ <<እኔ፡ ስለ፡ እነሱም፡ እለምናለሁ>>፡ ብሎ፡ ጸለየ፡ (ዮሐ.፲፯፥፱)። በጌቴሴማኒም፡ ተገኝቶ፡ <<አባ፡ ወአቡየ፡ ኵሉ፡ ይትከሀለከ፡ ወአሕልፋ፡ እምኔየ፡ ለዛቲ፡ ጽዋእ>>፦ <<አባ፡ አባት፡ ኾይ፣ ዅሉ፡ ይቻልሄል፣ ይህችን፡ ጽዋ፡ ከእኔ፡ አሳልፋት…>>፡ ብሎ፡ ጸለየ፡ (ማር.፲፬፥ ፴፮)። በመልእልተ፡ መስቀል፡ ተሰቅሎ፡ ሳለም፡ <<አባ፡ ሥሩይ፡ ሎሙ፡ እስመ፡ ዘእየአምሩ፡ ይገብሩ>>፦ <<አባት፡ ኾይ፡ የሚሠሩትን፡ አያውቁምና፣ ይቅር፡ በላቸው>>፡ ብሎ፡ ጸለየ፡ (ሎቃ.፳፫፥፴፬)።

ይህንን፡ የክርስቶስን፡ የሊቀ፡ ካህናትነት፡ አገልግሎት፡ ማለት፡ የአስታራቂነት፡ አገልግሎት፡ ለመግለጽ፡ ሐዋርያው፡ ቅዱስ፡ ዮሐንስ፡ በመልእክቱ፡ በምእራፍ፡ ኹለት፡ ላይ፡ ያለውን፡ ቃል፡ ጽፍአል። መናፍቃን፡ ግን፡ ሚሥጢሩን፡ ባለመገንዘብ፡ ይሰናከሉበታል፡ (ሉቃ.፪፥፴፬)። ስለተሰናከሉም፡ እየሱስን፡ አማላጅ፡ ይሉታል፤ ጌታችን፡ እየሱስ፡ ክርስቶስ፡ በጌቴሴማኒና፡ በመስቀል፡ ላይ፡ ሳለ፡ የፈጸመውን፡ የጸሎት፡ አገልግሎት፡ ማለት፡ የአስታራቂነት፡ አገልግሎት፡ ለምእመናን፡ ለማዘከር፡ ጽፎአል፡ (ሮሜ.፰፥፴፬፤ እብ.፭፥፯፤ ፱፥፲፭)።


ጌታችን፡ እየሱስ፡ ክርስቶስ፡ ከትንሣኤው፡ በፊት፡ በሰውነቱ፡ (በሥጋው)፡ የማስታረቅ፡ ማለት፡ የሊቀ፡ ካህናትነቱን፡ አገልግሎት፡ ማድረሱን፡ (መፈጸሙን)፡ ለመግለጽ፡ ቅዱሳን፡ ሐዋርያት፡ አመክንዮ፡ በተባለው፡ የቀኖና፡ ጸሎት፡ እንዲህ፡ ብለዋል፦ <<ወአረቀ፡ ትዝምደ፡ ሰብእ፡ ምስለ፡ እግዚአብሔር፡ ሊቀ፡ ካህናቱ፡ ሰብእ>>፦ (የአብ፡ ሊቀ፡ ካህናት፡ የሚሆን፡ ርሱ፡ እየሱስ፡ ክርስቶስ፡ የሰውን፡ ዘር፡ ከእግዚአብሔር፡ ጋር፡ አስታረቀ>>፡ ብለው፡ አስተምረዋል፡ (አመክንዮ፡ ዘሐዋርያት፡ ቊጥር፡ ፵፫)።

ስለዚህም፡ በሐዲስ፡ ኪዳን፡ መጻሕፍት፡ በአንዳንድ፡ ምእራፎች፡ <<ክርስቶስ፡ ሰገደ፣ ጸለየ፣ ለመነ…>>፡ ተብለው፡ የተጻፈው፡ ጌታችን፡ እየሱስ፡ ክርስቶስ፡ በመስቀሉ፡ የደኅንነትን፡ ሥራ፡ ከመፈጸሙ፡ በፊት፡ ስለ፡ እኛና፡ ስለ፡ መላው፡ ዓለም፡ ያደረገውን፡ (የፈጸመውን)፡ 

የሊቀ፡ ካህናትነትንና፡ የማስታረቅን፡ አገልግሎት፡ ለመግለጽ፡ ነው፤ ይኽውም፡ ሐዋርያው፡ ቅዱስ፡ ጳውሎስ፡ እንዳለው፦ <<ጌታችን፡ ኢየሱስ፡ ክርስቶስ፡ በእግዚAብሔር፡ ጸጋ፡ ስለ፡ ሰው፡ ዅሉ፡ ሞትን፡ ሊቀምስ፡ በፈቀደ፡ ጊዜ፡ (እብ.፪፥፱)፣ ያቀረቡለትን፡ ሆምጣጤ፡ ከቀመሰ፡ በኋላ፡ ><<ዅሉ፡ ተፈጸመ>>፡ ብሎ፡ በፈቃዱ፡ ነፍሱን፡ በሰጠ፡ ጊዜ፡ (ዮሐ.፲፱፥፴)፡ ሰው፡ ኾኖ፡ ወደ፡ ዓለም፡ የመጣበትን፡ የማስታረቅንና፡ የማዳንን፡ ሥራ፡ መፈጸሙን፡ አመልክቶአል። ከዚያች፡ የድኅነት፡ ቀን፡ ቀደም፡ ብሎም፡ ራሱ፡ ጌታችን፡ ስለዚህ፡ ሲናገር፦ <<አንሰ፡ ሰባሕኩከ፡ በዲበ፡ ምድር፡ ፈጺምየ፡ ግብረ፡ ዘወሀብከኒ፡ ከመ፡ እግበር>>፦ <<እኔ፡ ላደርገው፡ (ልሠራው)፡ የሰጠኸኝን፡ ሥራ፡ ፈጽሜ፡ በምድር፡ አከበርሁህ>>፡ ብሎአል፡ (ዮሐ.፲፯፥፫-፭)።

፲፪ኛ. ጌታችን፡ ኢየሱስ፡ ክርስቶስ፡ የማስታረቁንና፡ የማዳን፡ ሥራውን፡ ከፈጸመ፡ በኋላ፡ ስለ፡ ደቀ፡ መዛሙርቱና፡ ስለ፡ ዓለምም፡ ወደ፡ አብ፡ እንደማይለምን፡ (እንደማይጸልይ)፡ አስቀድሞ፡ ለደቀ፡ መዛሙርቱ፡ ነግሮአቸዋል፣ እንዲህ፡ ሲል፦ <<ወይእተ፡ አሚረ፡ ትሥእሉ፡ በስምየ፣ ወኢይብለክሙ፡ ከመ፡ አነ፡ ዘእስእሎ፡ ለአብ፡ በእንቲአክሙ፣ እስመ፡ ለሊሁ፡ አብ፡ ያፈቅረክሙ፡ ከመ፡ አንትሙኒ፡ አፍቀርክሙኒ፡ ወአምንክሙኒ፡ ከመ፡ እምኀበ፡ እግዚአብሔር፡ ወጻእኩ፡ ወመጻእኩ፡ ውስተ፡ ዓለም>>፦ <<በዚያን፡ ቀን፡ በስሜ፡ ትለምናላችሁ፣ እኔም፡ ስለ፡ እናንተ፡ አብን፡ እንደምለምን፡ የምላችሁ፡ አይደለሁም፣ እናንተ፡ ስለ፡ ወደዳችሁኝ፡ ከእግዚአብሔርም፡ ዘንድ፡ እኔ፡ እንደ፡ መጣሁ፡ ስላመናችሁ፡ አብ፡ ርሱ፡ ራሱ፡ ይወዳችኋልና፡ ከአብ፡ ወጥቼ፡ ወደ፡ ዓለም፡ መጥቻለሁ…>>፡ በማለት፡ እስተምሮአቸዋል፡ (ዮሐ.፲፮፥፳፮-፳፰)። እነሆ፡ ጌታችን፡ ኢየሱስ፡ ክርስቶስ፡ እንዲህ፡ ገልጾ፡ ማስተማሩን፡ እያነበቡ፡ መናፍቃን፡ ከትንሣኤና፡ ከእርገት፡ በኋላ፡ <<ኢየሱስ፡ ክርስቶስ፡ ይጸልያል፣ ይለምናል፣ ያስታርቃል፡ (ያማልዳል)>>፡ እያሉ፡ እንዴት፡ ያስተምራሉ? መናፍቃን፡ እንዲህ፡ ብለው፡ የሚያስተምሩትና፡ ሌላውን፡ የሚያስቱት፦

፩ኛ. ምሥጢረ፡ መጻሕፍት፡ ስለማያውቁ፣

፪ኛ. የክርስቶስ፡ አምላክነት፡ ስለሚንቁ፡ (ስለሚክዱ)፣

፫ኛ. በዚሁም፡ መሠረት፡ ሐዋርያው፡ ቅዱስ፡ ጴጥሮስ፡ <<ወእለስ፡ አልቦሙ፡ ትምህርት፡ ወእለ፡ ኢይሌብው፡ ይመይጥዎ፡ ለቃለ፡ መጻሕፍ፡ ከመ፡ ሜጥዎን፡ ለብዙኃት፡ መጻሕፍት፡ ለግኢዞሙ፡ ወያማስኑ>>፡ ሲል፡ እንዳስተማራቸው፡ ማለት፦ <<ሌሎች፡ ብዙዎችን፡ መጻሕፍትን፡ ለጥፋት፡ ወደ፡ ባሕላቸው፡ እንዳጣመሙአቸው፡ ያልተማሩና፡ የማያስተውሉ፡ ሰዎችም፡ የመጽሐፍን፡ ቃል፡ ወደ፡ ራሳቸው፡ ሐሳብ፡ ይለውጡታል>>፡ ሲል፡ እንዳስተማረው፡ የመጽሐፍን፡ ቃል፡ ወደ፡ ራሳቸው፡ እምነት፡ ስለሚለውጡት፡ ነው፡ (፪ጴጥ.፫፥፲፮)።

፲፫ኛ. እኛ፡ ግን፣ ጌታችን፡ ኢየሱስ፡ ክርስቶስ፡ ለደቀ፡ መዛሙርቱ፡ ሲነግራቸው፦ <<አኮኑ፡ ክርስቶስ፡ ሀለዎ፡ ይትቀተል፡ ወይባእ፡ ኀበ፡ ስብሐቲሁ>>፦ <<ክርስቶስ፡ መከራ፡ ይቀበል፡ ዘንድ፡ (ይሞት፡ ዘንድ)፡ ና፡ ወደ፡ ቀደመው፡ ክብሩ፡ ይመለስ፡ ዘንድ፡ ይገባው፡ የለምን?>>፡ ብሎ እንዳስተማራቸው፡ (ሉቃ.፳፬፥፳፭-፳፮)፣ ክርስቶስ፡ ወደ፡ ዓለም፡ የመጣበትንና፡ ሰው፡ የኾነበትን፡ የማዳን፡ ሥራውን፡ ፈጽሞ፡ በክብርና፡ በምስጋና፡ ወደ፡ ሰማይ፡ ካረገ፡ በኋላ፡ በእግዚአብሔር፡ አብ፡ ቀኝ፡ በክብርና፡ በምስጋና፡ ዙፋን፡ (መንበር)፡ ተቀምጦ፡ <<ይማለዳል፣ ይለመናል፣ የቅዱሳንን፡ ጸሎትና፡ ምልጃ፡ ይቀበላል፣ ይፈርዳል>>፡ ብለን፡ እናምናለን፤ እንዲህም፡ እናስተምራለን። ነገር፡ ግን፡ ሐዋርያው፡ ቅዱስ፡ ጴጥሮስ፡ እንዳስተማረው፡ (፪ጴጥ.፫፥፲፮)፣ የቅዱሳት፡ መጻሕፍትን፡ ቃል፡ በመለወጥና፡ በማጣመም፡ <<እየሱስ፡ ክርስቶስ፡ በሰማይ፡ ኾኖ፡ በእግዚአብሔር፡ ዘንድ፡ ስለ፡ ሰዎች፡ ይጸልያል፤ ያማልዳል…፡ ጠበቃ፡ ይሆናል>>፡ የሚሉት፡ ኹሉ፡ ልዩ፡ ወንጌል፡ መስበካቸውና፡ ልዩ፡ ትምህርት፡ ማስተማራቸው፡ ነውና፡ ቅዱስ፡ ጳውሎስ፡ እንዳስተማረው፡ የተለዩ፡ የተወገዙ፡ ናቸው፡ (ገላ.፩፥፭-፯)።

 

ክብረ ቅዱሳን ከሚለው አቡነ ገብርኤል በ1990 ካሳተሙት መጽኃፍ ተቀድቶ በ www.ethiopianorthodox.org ላይ የተለጠፈ።

Comments powered by CComment