ተወዳጆች እንደምን አላችሁ?
እንኳን አደረሳችሁ! 
ለምን አትሉም?
እሺ ለምን?
መጋቤ ምእመናን እና ወላዴ ሊቃውንት የሆነው የወለህ ነቅዐ ሕይወት ጉባኤ ቤት የልደት በዓል ነዋ!አሁን አራተኛ ዓመቱ ነው ይህ ጉባኤ ከተወለደ አራተኛ ዓመቱን እያከበረ ይገኛል በዚህ በልደቱ በዓልም የልደቴ እንዳትቀሩ ብሎ ከቤተ ክህነት ሠራተኛ እስከ መንግሥት ሠራተኛ እና መንፈሳውያን ማኅበራት ድረስ ለግለሰቦች ሳይቀር የጥሪ ደብዳቤ አድርሷል፡፡


በዚህም መሠረት ቀኑና ሰዓቱ ሲደርስ የተዘጋጀውን ጸበል ጸዲቅ ለማቅመስ በጸሎት ተባረከ ዳቦ ተቆርሶ ተሰጠ ቀጥሎም የጉባኤ ጸሎት ተደርጎ የመግቢያ መዝሙር ተዘመረ ቀጥሎም የእንኳን ደኅና መጣችሁ መልእክት ተላለፈ በመልእክቱም ውስጥ ስንኳን የጉባኤ ቤት ልደት ይቅርና የአንድ ሰው እንኳን ልደት በደመቀ ሁኔታ ሲከበር እናያለን ይህማ ምንኛ አይደምቅ የሚል አሳብ አዘል ጉዳይ አለው! በማስቀጠልም መርሐ ግብሩ መሪው ለዕለቱ መምህር ዐውደ ምህረቱን ለቀቀ 
መምህሩ ማን ናቸው አትሉኝም?
እሺ መምህሩ ማን ናቸው?
ከባሕር ዳር ጀምሮ የመጡ የሐዲሳት የመነኮሳት የሊቃውንት መምሕር የሆኑት መምህር አስተርአየ ናቸዋ!
ምን አሉ?
የትምህርታቸው መነሻ ክቡር ዳዊት የተናገረው
" ነኪር ነገሩ በእንቲአኪ ሀገረ እግዚአብሔር -
ሀገረ እግዚአብሔር ሆይ ስለ አንቺ የሚነገረው ድንቅ ነው" መዝ 86.4 በማለት ጀምረው አንደኛ የኢየሩሳሌምን ድንቅ የሚያስብል ምሥጢር ዳሰሱ
ሁለተኛ  የእመቤታችንን አስደናቂ የድንግልናና የእናትነት ሕይወት የአምላክ እናት መሆንዋን አሰረግጠው ተናገሩ 
በሦስተኛ የቤተ ክርስቲያንን ልዩ ምሥጢር አሳይተው 
በአራተኛውና በመጨረሻው የጉባኤ ቤትን ድንቅነት እንዲህ ሲሉ አሳይታዋል 
እመቤታችን ግሩም እሳተ መለኮትን እንደተሸከመች ጉባኤ ቤትም ግሩም ቃለ እግዚአብሔር የሚመሠጠርባት የሊቃውንት መፍለቂያ ናት ይህም ድንቅ ነው፡፡
 እውነት ነው ጉባኤ ቤት ድንቅ ያልሆነች ማን ድንቅ ይሆናል?
በቃ ምን ልበላችሁ ድንቅ በሆነ አንደበት ድንቅ ትምህርት ሰጥተዋል፡፡
በመቀጠልም ወረብ በመምህር ብርሃነ ሕይወት ተዘምሮ ቀጥታ ወደ ሪፖርት ተካሄደ ሪፖርቱን ያቀረቡት የጉባኤ ቤቱ ሊቀ ጉባኤ የሆኑት መምህር ዘመልአክ ዳግም ናቸው፡፡
 የቀረበውም በያዝነው ዓመት ምን ምን እንደተሠራና ምን ምን እንዳልተሠራ  ለታዳሚዎቹ የሚሳይ የተመጠነ ሪፖርት ነው፡፡ 
ቀጥሎ በመምህር ዕዝራ ቅኔ ቀረበ፡፡በመጨረሻ በነበረው መርሐ ግብር አስታያየትና ጥያቄ ከታዳሚዎች ተቀብሎ መርሐ ግብሩን በምሳ አጠናቀቀ፡፡
ስብሐት ለዘአብጽሐነ እምዝ
ከዚህ ለአደረሰን ምስጋና ይገባል
አብራችሁ እንደተሳተፋችሁ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ 
ቸር ሁኑ! 

"የመምህራን መብዛት ለዓለም መድኃኒት ነው"
መምህር መዝገበ ቃል ገብረ ሕይወት

Comments powered by CComment